በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ ባለዉ የዓለም ጤና ጉባኤ የጎንዮሽ መድረኮች በተለያዩ የጤና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዉይይት ተካሂዷል

  • Time to read less than 1 minute
#WHA79

በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ ባለዉ የዓለም ጤና ጉባኤ የጎንዮሽ መድረኮች የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በተገኙበት በተለያዩ ጤና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዉይይት ተካሂዷል።

ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ፣ ጊኒ፣ ኔፓል፣ እና አጋር አካላት ጋር በትብብር ባዘጋጀችዉ የጎንዮሽ መድረክ የድንገተኛ፣ ቀዶጥገና ህክምና አገልግሎትን በተመለከተ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ባጋሩት ገለጻ ታካሚን ማእክል ያደረገ የድንገተኛ ቀዶጥገና ህክምና አገልግሎት ማጠናከርና ተደራሽ ማድረግ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንና የጤና ዋስትናን ለማረጋገጥ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ዉይይት ድርጅቱ የካንሰር ህክምና እና የራዲዮቴራፒ አገልግሎት በኢትዮጵያ እንዲጎለብት ላደረገዉ የቴክኒክና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ ጤና ሚኒስቴር ይህን አገልግሎት ወደ ክልሎች እንዲስፋፋ እያደረገ ያለዉን ጥረት ድርጅቱ እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት በበኩላቸዉ የወባ እና የተዘነጉ ሀሩራማ በሽታዎችን ለማጥፋት የተያዘዉን ግብ ለማሳካት የድንበር ላይ ቅኝትና ቁጥጥር ስራን በማጠናከር የሀገራት በትብብር መስራት፥ የአዉቶኢሚዩን በሽታ (Autoimmune Disease) ህክምናን አስመልክቶ የሀገራት ተሞክሮ፣ የተቀናጀ የጤና ዋስትና እና ሰብአዊ አገልግሎት፣ ዲጂታል ጤና እንዲሁም ሌሎች የጤና ጉዳዮች በተካሄዱበት የጎንዮሽ መድረክ ላይ በመገኘት መልእክት አስተላልፈዋል።

#WHA79