"ጠንካራ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ሥርዓቶችን ለመገንባት ዲጂታል ጤናን ጥቅም ላይ ማዋል" በሚል መሪ ሃሳብ ሶስተኛው የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሃገራት የጤና መሪዎች የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ 

  • Time to read less than 1 minute
Consultation Forum

ሦስተኛው ዓመታዊ አውደ ጥናት፤ በምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ከፍተኛ የጤና፣ የገንዘብ እና  የኢንፎርሜሽንና የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ባለሥልጣናትን በመሰብሰብ አገራዊ ትብብርን ለማጠናከርና የጋራ የመማማሪያ መረብ ለመፍጠር ያለመ ነው። 


የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ ይበልጥ ፍትሃዊ፣ ጠንካራ እና በበጀት ረገድ ዘላቂነት ያለው የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል የጋራ ቀጠናዊ የዲጂታል ጤና ራዕይን ማምጣት መሆኑን ያስረዱት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ናቸው።


 ተሳታፊዎቹ በየአገራቱ ያለውን ተሞክሮ፣ የአፈጻጸም ማነቆዎችን እና የዲጂታል ጤና መፍትሔዎችን በሰፊው ተግባራዊ ለማድረግ የተገኙ ትምህርቶችን ይለዋወጣሉ፤ እንዲሁም ቴክኖሎጂ የጤና የሰው ኃይል አስተዳደርን እና የመረጃ ውህደትን እንዴት እንደሚያሳድግ ያላቸውን ቴክኒካዊ ግንዛቤ ያሳድጋሉ ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል። 


ዲጂታል ጤናን እና የርቀት ህክምናን (telemedicine) በሕክምና ትምህርታችን ውስጥ ማካተት: የጤና ክብካቤ ፋይናንስ እና የጤና ክብካቤ የሰው ኃይል ሥልጠናን ማሳደግ ይጠበቅብናል ሲሉ ዶ/ር መቅደስ ገልጸዋል።


አውደ ጥናቱ ቀደም ሲል በተደረጉ ውይይቶች ላይ የተነሱትንና በምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠና ያሉ የጤና ሥርዓቶች የሚጋፈጧቸውን ተጋላጭነቶች እንደ የልማት ዕርዳታ መቀነስ፣ የጤና መረጃ ሥርዓቶች ደካማነት እና የሰው ኃይል እጥረት ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እንደ ቁልፍ ማሻሻያ መፍትሔ አስቀምጧል። 


አውደ ጥናቱ በተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መካከል የሚኖርን ግንኙነት በማጎልበት  በአፍሪካ አህጉር ለሚደረጉ የዲጂታል ጤና ኢንቨስትመንቶች አስተዳደርን፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮችን፣ ፋይናንስን እና የረጅም ጊዜ ዘላቂነትን በጋራ ለማጠናከር ያለመ ነው።