ኢትዮጵያ በሕክምና ትምህርትና በዲጂታል ፈጠራ የአህጉራችንን የነገ ተስፋ ለመቅረጽ በቁርጠኝነት እየሠራች እንደምትገኝ የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው።
ሀገራችን ከራሷ አልፋ ከአፍሪካ ሀገራት የመጡ የጤና ባለሞያዎችን በከፍተኛ የሕክምና ትምህርት ተቋሞቿ በማስተማር እንደ ቀጣናዊ የልቀት ማዕከል እያገለገለች ትገኛለች ያሉት ክቡር አቶ ተመስገን፣ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መሪነት ሀገራችን በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በዲጂታል ፈጠራ የአህጉሪቱ ተምሳሌት ለመሆን ራሷን እያዘጋጀችም ነው ብለዋል።
በአፍሪካ አህጉራችን ውስጥ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎቻችን፣ ሆስፒታሎቻችን እና የኢንዱስትሪው ዘርፍ በጋራ ሊሠሩ፣ የምርምር ውጤቶችም የፖሊሲ መመሪያ ሊሆኑና የሕዝቡን ሕይወት በተግባር ሊለውጡ ይገባል ብለዋል ክቡር አቶ ተመስገን።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከመላው አፍሪካና ከሌሎች ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎችን በአዲስ አበባ መቀበሏ ክብር እንደሆነ ገልጸው፣የአፍሪካ ጤና ስርዓት ጥንካሬ የሚመሠረተው ብቁ፣ዘመናዊ እና ለወደፊት የተዘጋጀ የጤና ባለሙያ ኃይል በመፍጠር መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት፣ በዲጂታል ሽግግር፣ በአካባቢያዊ የመድኃኒትና የሕክምና ምርት ማምረት፣ በዘላቂ የጤና ፋይናንስ እና በጤና ባለሙያዎች ልማት ላይ ያስመዘገበችውን እመርታ ጠቅሰው የጤና ሙያ ትምህርትን ማጠናከር በአፍሪካ ጤና፣ ጽናትና የወደፊት እድገት ላይ የሚደረግ ወሳኝ ኢንቨስትመንት መሆኑን ገልጸዋል።