የሌሴቶ ንጉስ ግርማዊ ሌቲ ሳልሳዊ ከጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጋር በአዲስ አበባ በሚገኘው ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የህፃናት እንክብካቤ እና የስርዓተ-ምግብ ክፍልን ጎብኝተዋል፣ በጉብኝታቸው ኢትዮጵያ የእናቶችን እና የህፃናትን ጤና ለማሻሻል ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት ግርማዊ ንጉስ ሌቲ “ውጤታማ የስርዓተ-ምግብ እርምጃ ህይወትን ያድናሉ” በማለት አፅንኦት ሰጥተው፤ በኢትዮጵያ በስርዓተ-ምግብ ማሻሻያ እርምጃዎች በተሰራዉ ስራ ተምሳሌት የሚሆን ዉጤት ተገኝቷል ብለዋል። ስርዓተ-ምግብ በሽታን በመከላከል እና የህፃናትን ሞት በመቀነስ ረገድ ያለውን ወሳኝ ሚናም ገልጸዋል።
ንጉሱ እንዳሉት ኢትዮጵያ እናቶችን እና ህፃናትን ለመጠበቅ የምታደርገውን ጠንካራ ጥረት በገዛ ዓይናቸው ለማየት መቻላቸውን ተናግረው፤ አገሪቱ ስርዓተ-ምግብን ከጤና አጠባበቅ አደረጃጀቷ ጋር በማዋሃድ ዘላቂ የጤና ውጤቶችን ለማሳካት የሚያስመሰግን እና ስትራቴጂካዊ አቀራረብ መከተሏን ገልጸዋል።