የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) በመሆን የተሰጣቸዉን ኃላፊነት አስመልክቶ የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ከዶክተር ዣን ካሴያ ጋር ዉጤታማ  ውይይት አድርገዋል 

  • Time to read less than 1 minute
AI

በውይይታቸዉም በተለያዩ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን፤ በተለይም በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) በመሆን የተሰጣቸዉን አዲስ ኃላፊነት በሚመለከት በስፋት ተነጋግረዋል።


የፈጠራ ሥራዎች ለአፍሪካ ዕድገት ምንጊዜም ወሳኝ መሰረት ናቸዉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በጤናው ዘርፍ የሚገጥመንን ተለዋዋጭ ተግዳሮቶች ለመወጣት የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ዐቅም መጠቀም የጤና ሥርዓታችንን ለማጠናከር፣ ተደራሽነትን ለማስፋፋት እና ለሕዝባችን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ወሳኝ ነው ብለዋል። 


ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ ለአህጉሩ ለማካፈል እንዲሁም በፍጥነት ከሚለዋወጠው የቴክኖሎጂው ዓለም ጋር ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመራመድ የሚያስችሉ ጠንካራ አጋርነቶችን ለመመሥረት ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ርዕይ ወደ ተጨባጭና አካታች ውጤት ለመለወጥ ከአፍሪካ ሲዲሲ (Africa CDC) እና በመላው አህጉሪቱ ከሚገኙ አጋሮች ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ገልጸዋል።