የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በጉባኤው የመክፈቻ መልዕክታቸው ከ130 ዓመታት በፊት ቀደምት ኢትዮጵያውያን በዓድዋ በአይበገሬነት ያስመዘገቡት ድል፣ ዛሬ የሕዝባችንን ጤና በራስ አቅም የመጠበቅ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ መደገም አለበት ብለዋል።
የጤና ሉዓላዊነት ማለት መድኃኒቶችንና የሕክምና ቁሳቁሶችን በራሳችን የማምረት፣ የጤና ባለሙያዎቻችንን የማሰልጠንና የማቆየት፣ እንዲሁም ወረርሽኞችን ወይም የጤና ቀውሶችን የዓለምን እጅ ሳንጠብቅ በራሳችን የመቋቋም ብቃት መፍጠር መሆኑን አቶ ተመስገን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በጤናው ዘርፍ የግል ባለሀብቶች ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበው የሚሠሩበት አህጉራዊ መድረክ እንዲኖር፣ የአፍሪካ ጤና ፌዴሬሽን ዋና መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ እንዲመሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸዉ እንዳሉት የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በጉባኤው መሳተፋቸው ስለ የምስራቅ አፍሪካ የጤና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወያየት መሆኑን ገልጸዋል።
የጤና ስርዓታችን በድንበሮቻችን ውስጥ የተገደበ ቢሆንም፣ ፈተናዎቻችን ግን በድንበር የተገደቡ አይደሉም፤ ነገር ግን አንድነታችን እነዚህን ፈተናዎች ለመጋፈጥ ይረዳናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና ስርዓት መገንባቷን ያስረዱት ዶ/ር መቅደስ፤ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ስርዓታችንን ማጠናከር መቻላችን የእናቶች ህልፈትን ለመቀነስ አስችሎናል፤ ይህም ሊሆን የቻለው በመንግስት እና በግል ዘርፍ ትብብር ነው ብለዋል።
ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት የገለጹ ሲሆን፤ የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በጉባኤው ከተለያዩ አፍሪካ አገራት የመጡ ተሳታፊዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ አለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽን ተካሂዷል።