በስብሰባው ወቅት ሁለቱም ወገኖች በጤና ሚኒስቴር እና በድርጅቱ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነት ገምግመዋል፡፡ በተለይም በበሽታ መከላከል፣ ክትትል እና ማጥፋት ፕሮግራም ዘርፎች፣ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችን፣ የጊኒ ወርም በሽታን እና ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የጤና ጉዳዮች ጨምሮ ለተገኘው እድገት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።
ዶ/ር መቅደስ የካርተር ማዕከል እያደረገ ለሚገኘው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸው፤ ማእከሉ በመላ አገሪቱ የጤና ውጤቶችን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ መሆኑን ተናግረዋል። መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር በቅርበት ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት ያስታወቁ ሲሆን፤ ጥራት ያላቸውን አገልግሎቶች ተደራሽነት ለማስፋት በትብብር መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የካርተር ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ ፔጅ አሌክሳንደር ኢትዮጵያ በሽታን ለማጥፋት እና የጤና ስርዓትን ለማጠናከር የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። በጋራ ተነሳሽነቶች የተገኘውን እድገት አድንቀው፤ አገራዊ እና ዓለም አቀፍ የጤና ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ ትብብር አስፈላጊነትን አጉልተዋል።
የሁለትዮሽ ውይይቱ በአገሪቱ የጤና ዘርፍ እድገትን ለማፋጠን ያለመ በዲጂታል ጤና፣ በክትትል ስርዓቶች እና በአቅም ግንባታ ላይ የወደፊት ትብብር እድሎችን ዳስሷል።