የአፍሪካን የክትባት እና የሕክምና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያለመው ግዙፉ "ACHIEVE Africa" የተሰኘ ኢኒሼቲቭ ከ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በይፋ ተመሠርቷል 

  • Time to read less than 1 minute
Dr Mekdes Daba

​በኢኒሼቲቩ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት እ.ኤ.አ በ2040 የክትባት ፍላጎትን 60 በመቶ በአህጉር ውስጥ ለማሟላት ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች መሆኑን የገለጹ ሲሆን መንግስት የመድኃኒት ግዥ ስርዓቱን በአገር ውስጥ ለሚመረቱ ምርቶች ቅድሚያ እንዲሰጥ በማሻሻሉ፣ በዘርፉ የአገር ውስጥ ፍላጎትን ሽፋን ከ8 በመቶ ወደ 42 በመቶ ማደጉን ጠቁመው በቀጣይ አምስት ዓመታት ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
\
​ኢትዮጵያን የፈጠራ ማዕከል (Innovation Hub) ለማድረግ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር መቅደስ የሀገሪቱ የክትባት የማምረት ጉዞ አሁን ላይ "ይሳካል ወይ?" የሚለው ጥያቄ ቀርቶ "እንዴት እና በምን ፍጥነት?" ወደሚለው ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩን አስታውሰዋል። 

ይህ ጉዞ ኢትዮጵያ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በአፍሪካ አጀንዳ 2063 የተቀመጠውን ራስን የመቻል ራዕይ ለማሳካት ያላትን ቁርጠኝነትና ዝግጁነት የሚያሳይ መሆኑንም አክለው የገለፁ ሲሆን ​ይህ ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክት የተቀናጀ የክትባትና የባዮሎጂካል መድኃኒቶች ምርት በአፍሪካውያን እውቀትና ጥረት እንዲከናወን በማስቻል፣አህጉሪቱ የወደፊት የጤና ተግዳሮቶችን በራሷ አቅም እንድትቋቋም ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

የኢኒሼቲቩ ዋና ግብ አፍሪካ የክትባት ማሸጊያ ማዕከል ብቻ ሳትሆን የክትባት ግኝትና ምርምር መነሻም እንድትሆን ማስቻል እና ከክትባት ግኝትና ከክሊኒካዊ ሙከራ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ስርጭት ያለውን አጠቃላይ የእሴት ሰንሰለት (End-to-End Ecosystem) በአህጉሪቱ ለመገንባት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተገልጿል።

​ይህ ፕሮጀክት የአፍሪካ ሳይንቲስቶች የራሳቸውን የምርምር እና ልማት (R&D) ስራ እንዲመሩ ለማስቻል አስፈላጊውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ከማምጣትም በላይ በክትባትና ሕክምና ዘርፍ የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን አፍሪካ ራሷን እንድትችልና የዜጎቿን የጤና ዋስትና በዘላቂነት እንድታረጋግጥ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።