በኢትዮጵያ በስርዓተ-ምግብ ማሻሻያ እርምጃዎች በተሰራዉ ስራ ተምሳሌት የሚሆን ዉጤት ተገኝቷል - የሌሴቶ ንጉስ ግርማዊ ሌቲ ሳልሳዊ

  • Time to read less than 1 minute
nutrition

የሌሴቶ ንጉስ ግርማዊ ሌቲ ሳልሳዊ ከጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጋር በአዲስ አበባ በሚገኘው ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የህፃናት እንክብካቤ እና የስርዓተ-ምግብ ክፍልን ጎብኝተዋል፣ በጉብኝታቸው ኢትዮጵያ የእናቶችን እና የህፃናትን ጤና ለማሻሻል ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት ግርማዊ ንጉስ ሌቲ “ውጤታማ የስርዓተ-ምግብ እርምጃ ህይወትን ያድናሉ” በማለት አፅንኦት ሰጥተው፤ በኢትዮጵያ  በስርዓተ-ምግብ ማሻሻያ እርምጃዎች በተሰራዉ ስራ ተምሳሌት የሚሆን ዉጤት ተገኝቷል ብለዋል። ስርዓተ-ምግብ በሽታን በመከላከል እና የህፃናትን ሞት በመቀነስ ረገድ ያለውን ወሳኝ ሚናም ገልጸዋል። 

ንጉሱ እንዳሉት ኢትዮጵያ እናቶችን እና ህፃናትን ለመጠበቅ የምታደርገውን ጠንካራ ጥረት በገዛ ዓይናቸው ለማየት መቻላቸውን ተናግረው፤ አገሪቱ ስርዓተ-ምግብን ከጤና አጠባበቅ አደረጃጀቷ ጋር በማዋሃድ ዘላቂ የጤና ውጤቶችን ለማሳካት የሚያስመሰግን እና ስትራቴጂካዊ አቀራረብ መከተሏን ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ሆስፒታሉ የኢትዮጵያን የህፃናት እንክብካቤ እና ስርዓተ-ምግብ  ቅድሚያ ለመስጠት ያላትን ራዕይ እና ቁርጠኝነት ያንፀባርቋል ብለዋል። ስርዓተ-ምግብ በጤናው ዘርፍ ብቻ የሚስተናገድ ሳይሆን ከሴክተር መስሪያቤቶችና ባለድርሻ አካላት በትብብር በሚያደርጉት የተቀናጀ እርምጃ እንደሚተገበር ገልጸዋል።

"ስርዓተ-ምግብ  እና የህፃናትን ህልውና ማሳደግ የአገራችንን የሰው ልጅ ካፒታል መሰረት መገንባት ነው" ሲሉ ዶ/ር መቅደስ ተናግረዋል። ስርዓተ-ምግብ በኢትዮጵያ የልማት አጀንዳ ውስጥ ማዕከላዊ ሆኖ መቀመጡ ጤናማ እና ውጤታማ የወደፊት ትውልድን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

ሚኒስትሯ ሆስፒታሉን በመጎበኘታቸው ለግርማዊነታቸው ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የሌሴቶ የህፃናት እንክብካቤ እና ስርዓተ-ምግብ ልምድ በማጋራት በጋራ በትብብር እንደሚሰራ ያላቸዉን እምነት ገልጸዋል።