ኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባት እንዲከተቡ አድርጋለች!
የ2ኛ ዙር የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ ሁለተኛ ዙር የኮቪድ 19 ክትባት ዘመቻ በአገር አቀፍ ደረጃ ከየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን በአሁኑ ዘመቻ የተሰጠውን ከ14 ሚሊዮን በላይ ክትባትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መከተብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ከሆነ 17 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ክትባት የወሰዱ ሲሆን ከአንድ መቶ ዘጠና ሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑት የማጠናከርያ ክትባቱን (Booster dose) ተከትበዋል፡፡ በጥቅሉ ከ25 ሚሊዮን በላይ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውልም ተደርጓል፡፡
በዘመቻውም በመጀመርያው ዙር የመከላከያ ክትባቱ ያልተሰጠባቸው የአማራ እና የአፋር ክልሎችን በማካተት ክትባቱን መስጠት መቻሉንም ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡