የአፍሪካ የሕክምና ትምህርት (MedEDAfrica 2026) ኮንፈረንስ በስኬት ተጠናቀቀ!

  • Time to read less than 1 minute
MedEDAfrica 2026

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካን የሕክምና ትምህርት ማዘመን ላይ ያተኮረው የ"MedEDAfrica 2026" ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ዛሬ ተጠናቋል። 


በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ የሕክምና ትምህርትን ማጠናከርና የጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባት የጤና አገልግሎት ጥራትና ደህንነትን ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያም የሥልጠና ጥራትንና የባለሙያዎችን ተደራሽነት ለማሳደግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን አስታውሰዋል።


ወ/ሮ ሳህረላ ኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን ቁጥር፣ ተደራሽነትና የሥልጠና ጥራት ለማሳደግ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመተግበር የጤና ሥርዓቱን እያጠናከረች መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ በተጨማሪም የጎረቤት ሀገራት የሕክምና ተማሪዎችን በሬዚደንሲ ፕሮግራም በማሰልጠን የክልሉን የጤና ሰው ኃይል ልማት እየደገፈች መሆኑን አስታውቀዋል።


የMedEDAfrica ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሊዮኔል ግሪን-ቶምፕሰን ኢትዮጵያ ለጉባዔው ስኬት ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበው፣ በጤና ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ጠቃሚ የልምድ ልውውጥ መደረጉን ገልጸዋል።


ጉባዔውም በአፍሪካ ደረጃ ብቁ የጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት፣ የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል እና የአህጉሪቱን የጤና ሥርዓት በጋራ ለማጠናከር የሚያግዙ አህጉራዊ ስትራቴጂዎችና ሀሳቦች ላይ ጥልቅ ውይይት መካሄዱን አስታውቀዋል።


በመጨረሻም ለጉባኤው መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና የተሰጠ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ ከፕሮግራሙ መጠናቀቅ በኋላ የአድዋ ሙዚየምን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡትን የወንዝ ዳርና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።