በኢትዮጵያ በአዲስ ቴክኖሎጂ ህክምና የሚሰጥ የመጀመሪያው የስትሮክ ህክምና ማእከል በዛሬው እለት ተመርቆ ተከፍቷል።

  • Time to read less than 1 minute
stroke treatment center

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሠ በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንዳሉት የጤናው ዘርፍ በርካታ መሻሻሎች እያሣየ ያለ ቢሆንም ገና ብዙ ወደ ፊት መሄድ ይጠበቅበታል ብለዋል። የአክሶል ስትሮክ እና ስፓይን ማእከል መከፈቱ እንደ ሀገር የእስትሮክ ህክምናን አንድ ምእራፍ ወደ ፊት የሚወስድ መሆኑን ጠቅሰው ማእከሉ  ለዚህ ምረቃ በመድረሱ ያላቸውን አድንናቆት ገልጸዋል። ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ እና የተለየ አገልግሎት ይዞ የመጣ ማእከል በአገሪቱ መከፈት መቻሉ ለጤናው ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።


ላለፋት አመታት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እና በዚህ ሳቢያ የሚመጣ ሞት እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ዶክተር ሊያ ይህን ችግር ለመቅረፍ የጤና ሚኒስቴር ከመከላከል ስራው ጎን ለጎን የስፔሻሊቲ ህክምና አገልገግሎት ማስፋፋት ስራ የሚያሰራ የአስር አመት ፍኖተ ካርታ  ተዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑን አስረድተዋል።


ዶ/ር ሊያ መንግስት የመጀመሪያና አጠቃላይ ሆስፒታሎች ኢንቨስት ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንና የስፔሻሊቲ አገልግሎት ማስፋፋት ላይ ከመንግስት ባሻገር የግሉ ዘርፍ ጠንካራ ተሣትፎ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል። ለዚህም መንግስት ለግሉ ዘርፋ ምቹ  ሁኔታ የመፍጠርና  የማመቻቸት ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።


የአክሶል ስትሮክ እና ስፓይን ማእከል አጋር መስራች የሆኑት ዶክተር አከዛ ጠአመ የአክሶል ስትሮክና ስፓይን  ማእከል በአገራችን እስከዛሬ ያልነበረ አዲስ አገልግሎት የሚሰጥ  መሆኑ ለየት ያደርገዋል ያሉ ሲሆን ለአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት አገራት የሚመጡትንም የሚታከሙበት ተቋም እንደሆነም ገልጸዋል። ላለፋት አስር አመታት በላይ በኢትዮጵያ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት ከአሜሪካን ሜዲካል ማእከል፣ ሰማሪታን የቀዶጥገና ማእከል አሁን ደግሞ አክሶል የስትሮክ እና ስፓይን ማእከል እነዚህ ሶስት ተቋማት ለአገሪቱ ጤና ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት የሚሠሩ ተቋማት መሆናቸው የገለጹት ዶክተር አከዛ ከዚህም  የበለጠ ስራ ለመስራት በዝግጅት ላይ እንደሆኑም አስታውቀዋል።


 በአለም ካለዉ የስትሮክ መጠን ውስጥ ሁለት ሶስተኛው የሚገኘው በታዳጊ አገራት ሆኖ አምራች አድሜ ክልል ወስጥ ያሉትን እያጠቃ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የአክሶል ስትሮክ እና ስፓይን ማእከል አጋር መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ወንድወሰን ገብረ አማኑኤል ሲሆኑ የበሽታው በአገሪቱ መስፋፋት ለማእከሉ መመስረት በምክንያትነት አቅርበዋል። ድንገተኛ ታሞ የመጣ ታማሚ ከአምቡላንስ በድንገተኛ ክፍል ተቀብሎ እርዳታ የሚሰጥበት፣  ታካሚው በተኛበት ክብደቱን የሚለካ አና ሌሎችም አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አልጋ ያላቸው ክፍሎች ማመቻቸት መቻሉን ዶክተር ወንደወሠን የገለጹ ሲሆን ካት ላብ የተባለ መሳሪያ ያለው ክፍል ውስጥ የስትሮክ ህመሙን ከመለየት እስከ ማከም የሚቻልበት አገልግሎት በአንድ ጣሪያ የሚያገኙበት እንዲሁም ታካሚዎች በማገገሚያ ክፍል ልዩ ልዩ የፊዝዮቴራፒ  አገልግሎት የሚሰጥበት ማእከል እንደሆነም በገለጻቸው አቅርበዋል።


ዶክተር ሊያ የህክምና ማእከሉን በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን የድንገተኛ ክፍል፣ የጽኑ ህክምና  መኝታ ክፍሎች፣ የሲቲ እስካን የአንጎል ቀዶጥገና ክፍል፣ የካት ላብ፣ የቴክኒካል እና መቆጣጠሪያ ክፍሎችን እየተዘዋወሩ ጎብኝተዋል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የስትሮክ ማእከል በዛሬው እለት ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን ማእከሉ በአፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ሁለተኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ የመጀመሪያው የእስትሮክ ማእከል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የስትሮክ እና ስፓይን ማእከሉ ለየት ያለና አዲስ ቴክኖሎጂ ባፈራቸው በርካታ የህክምና መሳሪያዎች እና ባለሙያዎች የተደራጀ ነው።