Articles

"የእናቶችን ሞት ለማስቀረት ሁሉም አካላት ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ ሊሰሩ ይገባል!" ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ

Dr. Dereje Duguma

"በማንኛውም ሁኔታ ከወሊድ በሁዋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንግታ" በሚል መሪ ቃለ በአማራ ክልላዊ መንግስት ደሴ ከተማ በተከበረበት ወቅት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደተናገሩት በሀገራችን በቀን ከሰላሳ በላይ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ተናግረው እንደ ደሴ ባሉ በህውሀት አሸባሪ ቡድን የጦርነት ጥቃት እና ዘረፋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ችግሩ ሊከፋ እንደሚችል በመረዳት ሁሉም አካላት በከፍተኛ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

 
አሸባሪው ብድን የጤና ተቋማቱን ቢያወድሙና ቢዘርፉም ጠንካራ መንፈሳችንን ግን ሊነኩት አይቻላቸውምና ደግመን ተረባርበን በመገንባት ለእናቶችና ለሌሎችም የጤና አገልግሎቶችን በተሻለ እናቀርባለን ብለዋል፡፡  

የኮቪድ 19ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚያግዝ ሰው ሰራሽ መተንፈሻ መሳሪያ ድጋፍ ርክክብ ተደረገ

Delivery

ግምታቸው 30 ሚሊዮን ብር የሚሆን 100 ሰው ሰራሽ መተንፈሻ መሳሪያዎች የኮቪድ 19ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚያግዝ ሰው ሰራሽ መተንፈሻ መሳሪያ ድጋፍ ለጤና ሚኒስቴር ተደርጓል፡፡

 
ድጋፉን ለጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ  ያስረከቡት የሞደርን ኢ.ቲ.ኤች አውት ሶርስ ፒ.ኤል.ሲ ተወካይ የሆኑት አቶ ታዲዮስ ተፈራ፤ ድጋፉ የተደረገው በኮቪድ የተጠቁ ዜጎችን ለመርዳት ታስቦ መሆኑን ገልጸው ድጋፋቸው የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 
 የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ፣ ድጋፉን ያደረጉትን ድርጅቶች አመስግነው፤ መሳሪያዎቹ በጽኑ ህሙማን ማገገሚያ የሚገኙ ታካሚዎችን ለመርዳት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸው ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

"እናቶች በጤና ተቋማት በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲወልዱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት።"  ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ

Dr. Dereje Duguma

የጤናማ እናትነት ወር "በማንኛውም ሁኔታ ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶችን ሞት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንግታ" በሚል መሪ ቃል በአለም ለ35ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስተባባሪነት በአበበች ጎበና የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል ተከብሯል፡፡ 


የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በዓሉን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር በሀገራችን ከእናቶች ሞት ጋር ተያይዞ በተደረገው ጥናት በዓመት ከሚሞቱት እናቶች በተለይ 50 በመቶ የሚሆኑት ከደም መፍሰስ ጋር በተያያዘ ምክንያት መሆኑን ገልፀው እናቶች በጤና ተቋማት በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲወልዱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡ ለዚህም የሃይማኖት አባቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የኪነጥበብ ሰዎች፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ በመፍጠር እናቶች በህክምና ተቋም እንዲወልዱ እንዲያበረታቱ አሳስበዋል፡፡