በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካን የሕክምና ትምህርት ማዘመን ላይ ያተኮረው የ"MedEDAfrica 2026" ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ዛሬ ተጠናቋል።
በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ የሕክምና ትምህርትን ማጠናከርና የጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባት የጤና አገልግሎት ጥራትና ደህንነትን ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያም የሥልጠና ጥራትንና የባለሙያዎችን ተደራሽነት ለማሳደግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን አስታውሰዋል።
ወ/ሮ ሳህረላ ኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን ቁጥር፣ ተደራሽነትና የሥልጠና ጥራት ለማሳደግ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመተግበር የጤና ሥርዓቱን እያጠናከረች መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ በተጨማሪም የጎረቤት ሀገራት የሕክምና ተማሪዎችን በሬዚደንሲ ፕሮግራም በማሰልጠን የክልሉን የጤና ሰው ኃይል ልማት እየደገፈች መሆኑን አስታውቀዋል።