Articles

ኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባት እንዲከተቡ አድርጋለች!

Dr. Tegene Regassa

የ2ኛ ዙር የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ ሁለተኛ ዙር የኮቪድ 19 ክትባት ዘመቻ በአገር አቀፍ ደረጃ ከየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን በአሁኑ ዘመቻ የተሰጠውን ከ14 ሚሊዮን በላይ ክትባትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መከተብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡


እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ከሆነ 17 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ክትባት የወሰዱ ሲሆን ከአንድ መቶ ዘጠና ሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑት የማጠናከርያ ክትባቱን (Booster dose) ተከትበዋል፡፡ በጥቅሉ ከ25 ሚሊዮን በላይ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውልም ተደርጓል፡፡  


በዘመቻውም በመጀመርያው ዙር የመከላከያ ክትባቱ ያልተሰጠባቸው የአማራ እና የአፋር ክልሎችን በማካተት ክትባቱን መስጠት መቻሉንም ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡ 

በሶማሌ ክልል በድርቅ የተጎዱ አከባቢዎች ለሚገኙ ጤና ተቋማት አገልግሎት የሚውል ሰላሳ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያዩ መድሀኒቶች፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል። 

donation

በጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰሀረላ አብዱላሂ የተመራ ከጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት እና የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት የተውጣጣ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ቡድን በሶማሌ ክልል በድርቅ የተጎዱ አከባቢዎች ለሚገኙ ስድስት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና ስድስት ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት የሚውል የመድሀኒት፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የህክምና ቁሳቁሶችን  አስረክቧል። 


ሰላሳ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት መድሀኒት፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የህክምና ቁሳቁሶች በሁለት ዙር በክልሉ ጤና ቢሮ በኩል ወደ ጤና ተቋማት የሚደርስ ርክክብ ተደርጓል። 


በቀጣይም በድርቅ ለተጎዱ የኦሮሚያ፣ ደቡብ ብ/ብ/ህ/ክ እና ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የምግብና መድሀኒት አቅርቦት እንደሚቀጥል ወ/ሮ ሰሀረላ ገልጸዋል።

በጤና ሚኒስቴር እና ግብርና ሚኒስቴር የሚመራ የዓለም ጤና ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅትን እንዲሁም ዩኒሴፍን ያካተተው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በዛሬው እለት በኦሮሚያ ክልል በድርቅ የተጎዳዉን የቦረና ዞንን ጎብኝቷል። 

Borena

በዱቡሉቅ ወረዳ የዱቡሉቅ ጤና ጣቢያ አጣዳፊ የምግብ እጥረት ህክምና መስጫ ማዕከልንና የመጠጥ ውሃ ጥራት ቁጥጥርን እንዲሁም በድርቁ የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን ቡድኑ ተመልክቷል። 


በጉብኝቱም ቡድኑ ከዞኑ አመራሮች ጋር በወቅታዊዉ ሁኔታና የድንገተኛ ድጋፍ አሰጣጥን አስመልክቶ ውይይት ያደረገ ሲሆን በድርቁ የተጎዱ እና የጤና እና የምግብ እጥረት ጉዳት የደረሰባቸዉን ዜጎች ለማከም፤ ለመደገፍ የሚዉሉ ከአለም ጤና ድርጅት የተገኙ 31 ሜትሪክ ቶን የድንገተኛ ህክምና ቁሳቁስ ድጋፎችንም አበርክቷል።


በቀጣይም ክፍተት ባለባቸው ላይ የፌደራል መንግስትና አጋር አካላትና ድጋፉን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።