በውይይታቸዉም በተለያዩ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን፤ በተለይም በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) በመሆን የተሰጣቸዉን አዲስ ኃላፊነት በሚመለከት በስፋት ተነጋግረዋል።
የፈጠራ ሥራዎች ለአፍሪካ ዕድገት ምንጊዜም ወሳኝ መሰረት ናቸዉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በጤናው ዘርፍ የሚገጥመንን ተለዋዋጭ ተግዳሮቶች ለመወጣት የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ዐቅም መጠቀም የጤና ሥርዓታችንን ለማጠናከር፣ ተደራሽነትን ለማስፋፋት እና ለሕዝባችን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ ለአህጉሩ ለማካፈል እንዲሁም በፍጥነት ከሚለዋወጠው የቴክኖሎጂው ዓለም ጋር ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመራመድ የሚያስችሉ ጠንካራ አጋርነቶችን ለመመሥረት ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ርዕይ ወደ ተጨባጭና አካታች ውጤት ለመለወጥ ከአፍሪካ ሲዲሲ (Africa CDC) እና በመላው አህጉሪቱ ከሚገኙ አጋሮች ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ገልጸዋል።