በአፍሪካ የህፃናት ጤና እና ስርዓተ-ምግብ ላይ ያተኮረው መድረክ የአፍሪካ ህብረት የስርዓተ-ምግብ ሻምፒዮን የሆኑት የሌሶቶ ግርማዊ ንጉሥ ሌቲ ሳልሳዊ፣ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፣ ኢትዮጵያ የሌማት ቱሩፋት እና የአረንጓዴ ሌጋሲ አስርት ዓመታት ተነሳሽነቶችን በተሳካ ሁኔታ በመተግበር ጉልህ ውጤቶችን ማስመዝገባን ተናግረዋል።
እንደ አቶ አደም ገለጻ፣ ፕሮግራሞቹ በመላ አገሪቱ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እናቶችንና ህጻናትን የተመጣጣኝ ምግብ አቅርቦትን በማሻሻልና የመቋቋም አቅምን በማጠናከር ተጠቃሚ አድረገዋል።
መንግስት የተመጣጠነ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠው፣ ቀጣይነት ያለው ጥረት የወደፊት ትውልድ ደህንነትን ለመጠበቅ እንደሚያስችል አፅንዖት ሰጥተዋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ፣ የሀገር ውስጥ ፋይናንስን እንዲያጠናክሩ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተቀናጀ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ያቀረቡት አደም ፋራህ፤ በዚህም የአፍሪካ ብልጽግና መሰረት የሆነውን የሰው ኃይል በጋራ ማልማት እንደሚቻል ተናግረዋል።
ሃገራት የተሻለ የስርዓተ-ምግብ ፕሮግራሞችን እንዴት መተግበር እንዳለባቸው እና የኢትዮያን ተሞክሮ ያጋሩት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ፤ የህጻናት ጤናን በማሻሻል፣ የሰቆጣ ቃልኪዳንን በመተግበር እና የቀዳማይ ልጅነት ልማትን በመተግበር የተገኘውን አበረታች ውጤት አስረድተዋል፡፡
በመድረኩም የቀድሞ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የያዳም ፋውንዴሽን መስራች ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ባደረጉት ንግግር በአህጉሪቱ የህፃናትን አመጋገብ እና የሰው ሀብት ልማትን ለማሳደግ የፖለቲካ አመራር፣ ዘላቂ ፋይናንስ እና የአየር ንብረት ምላሽ ሰጪ ስልቶች አስፈላጊነትን አፅንዖት ሰጥተዋል።።
በመድረኩ በአፍሪካ ስርዓተ-ምግብን ለማሻሻል የሚረዳ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በአፍሪካ ህብረት እና በኑትሪሽን ኢንተርናሽናል ተፈርሟል፡፡