የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ 5ኛው ዓለም ዓቀፍ የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና ጉባዔ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በአፍሪካ ህብረት እና በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ወደተዘጋጀው ጉባኤ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
ለጤና ያለን ኃላፊነት የሚጀምረው ህሙማን ክሊኒክ ከመድረሳቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው፤ ይኸውም በንጹህ ውሃ፣ በተመጣጠነ ምግብ እና ህጻናት የሚያድጉበት ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ በማመቻቸት መሆኑን ዶ/ር አብይ በመድረኩ አስረድተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት እና የሙቀት መጠን መጨመር በሽታዎች ሊሰራጩ እንደሚችሉ እና ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ያብራሩት ዶ/ር አብይ፤ ለሁሉም ህዝቦች የጤና ዋስትና እና ሉዓላዊነት ማለት በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥም ሆነ በችግር ጊዜ ሊተማመኑበት የሚችል ስርዓት መገንባት ማለት መሆኑን አጽንኦት ተሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብራችን መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ወደ እያንዳንዱ ቤተሰብ አቅርቧል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች በመላ ሀገሪቱ ማህበረሰቡን እያገለገሉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ቤተሰቦችን ከህመም ጋር ተያይዞ ከሚመጣ የገንዘብ ጫና ለመጠበቅ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓታችንን ማስፋፋታችንንም በመድረኩ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ለመድሃኒቶች እና ለክትባቶች ቁጥጥር የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የብስለት ደረጃ 3 (Maturity Level 3) መግኘታችንንም አስታውሰዋል። ይህም ለአምራቾቻችን ኢትዮጵያን እና ቀጠናውን ለማገልገል ጠንካራ መሰረት ይሰጣቸዋል ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት በአህጉራችን ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) እና ዲጂታል ጤናን የማስፋፋት ኃላፊነት እንደሰጣቸው የተናገሩት ዶ/ር አብይ፤ የኢትዮጵያ አካሄድም ዲጂታል ጤናን የዕለት ተዕለት የሕክምና አገልግሎት አካል ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።