የኢትዮጵያ የውስጥ ደዌ ህክምና ማህበር 7ኛው ዓመታዊ ሳይንሳዊ ጉባኤ ተካሄደ

  • Time to read less than 1 minute
group picture

በእለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የኢትዮጵያ ጤና ፖሊሲ በማህበረሰብ ጤና ማጎልበት፣ በሽታ መከላከልና የጤና አገልግሎት ሽፋን ማሻሻል ላይ ትኩረት አደርጎ የተሰራበት እና በዚህም ብዙ ስኬቶች  የተመዘገቡበት እንደነበር የተናገሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን የተላላፊ በሽታዎች ብቻ ሳይሆኑ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እና አደጋዎችም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን ተከትሎ የከፍተኛ የፈውስ ህክምና ፍላጎትም እንዲሁ የጨመረበት ወቅት በመሆኑ የጤና ሚኒስቴር ለዚሁ ምላሽ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሶስተኛ ደረጃ /tertiary care/  አገልግሎት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ 


በሆስፒታሎቻችን በሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች በአገልግሎት ሽፋን  እና ጥራት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እየታዩ ቢሆንም ህብረተሰቡ ከሚፈልገው አንፃር ግን ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን የገለጹት ዶክተር አየለ በጤና ሙያተኞች ስብጥርና ስርጭት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ፍሰትና ቅልጥፍና፣ በህክምና መሳሪያዎች ማኔጅመንት ስርአት፣ በግብአት አቅርቦት መቆራረጥና ብክነት  እንዲሁም በሌሎች በርካታ የጤናው ስርዓት  ክፍተቶች ምክንያት አሁንም የተገልጋይ እርካታን በሚፈለገው ደረጃ ማድረስ እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡


ይህንንም ለማሻሻልና በዘላቂነት ለመፍታትም ጠንካራ የጤና ስርኣት መዘርጋትን ጨምሮ  ውጤታማ የሀብት አጠቃቃም ስርዓትን መተግበር እና አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችና ቴክኖሎጂን መጠቀም ብሎም ከውጭ እና ከአገር ወስጥ አጋሮች ጋር በትብብር መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።  


በዚህም የጤና ሚኒስቴር የ3ኛ ደረጃ /tertiary care/ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችል ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ  በተመረጡ እና ቅድሚያ በሚሹ የጤና ችግሮች ዙሪያ መተግበር የጀመረ መሆኑን ዶክተር አየለ የገለጹ ሲሆን በዚህ ረገድ የሙያ ማህበሩ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

      
የኢትዮጵያ የውስጥ ደዌ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ሲሳይ ስርጉ እንዳሉት የውስጥ ደዌ ህክምና ማህበር የአባላቱን ሙያዊ መብቶች እንዲጠበቁ፣ የአባል ሙያተኞችን እውቀት፣ ግንዛቤና ክህሎት የማሻሻል ስራ በመስራት፣ የውስጥ ደዌ ጤና ህክምና ጥራቱን ለማስጠበቅና ዘመኑ የደረሰበት ደረጃ ለማድረስ፣ በአገራዊ የሳይንስ ጥናትና ምርምር በመደገፍ ሙያዊ ስነምግባር የተላበሰ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለማድረስ ብሎም በጤናው ዘርፍ ከሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር መስራትን ዓላማ ያደረገ ማህበር ሲሆን እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ከዋናው ስራ አስፈጻሚ በተጨማሪ 16 ቅርንጫፍ ቢሮዎችን አደራጅቶ የአባላቱን አቅም በማጎልበት የድህረ ምረቃ ስልጠና እና ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና የማመቻቸት፣ የስልጠና አተገባበር ላይ ተከታታይ የድጋፍ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑ ገልጸዋል፡፡


የዘንድሮው ጉባኤ ‹‹Tertiary care in Ethiopia challenges & opportunities›› በሚል ዋና ርእስ የሚካሄድ ሲሆን በተለያዩ የውስጥ ደዌ የሙያ መስኮች ላይ ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች  በተመረጡ ሁለት የጤና ችግሮች እና ህክምናዎች ዙሪያ ላይ ሰፊ ገለጻ የሚቀርብ ሲሆን ሶስት የምርምር ውጤቶችም ቀርበው ውጤታማ ውይይት ተደርጎ ለቀጣይ ስራ የሚረዱ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት እንደሚሆን ዶክተር ሲሳይ ተናግረዋል፡፡


በመድረኩ ከየህክምና ትምህርት ቤቱ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ የውስጥ ደዌ ተመራቂ ሬዚደንት ሃኪሞች የተሸለሙ ሲሆን ከውስጥ ደዌ ህክምና ጋር ተያያዥነት ያላቸው የመድሃኒት፣ የግብአትና አገልግሎት አቅራቢ አጋር ድርጅቶች አውደ ርእይም ተካሂዷል፡፡