አባቶች፣ የቤተሰብ አባላትና ማህበረሰቡ ለሚያጠቡ እናቶች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል

  • Time to read less than 1 minute
group picture

"ምቹ ሁኔታ ለሚያጠቡ እናቶች፣ እናስተምር፣ እንደግፍ!!" በሚል መሪ ቃል በአለም ለ30ኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ የጡት ማጥባት ሳምንት እየተከበረ ሲሆን ዛሬ በደብረብርሃን ወይንሸት የተፈናቃዮች መጠለያ ከሚገኙ እናቶችና ህጻናት ጋር በአሉ ተከብሯል። 


በጤና ሚኒስቴር ሃገር አቀፍ የስርዓተ ምግብ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ህይወት ዳርሰኔ በስነስርዓቱ ላይ እንደ ተናገሩት እናቶች ልጆቻቸውን እስከ ስድስት ወራት ጡት ብቻ ማጥባታቸው የህጻኑን ጤንነት ከመጠበቅና የተስተካከለ እድገት እንዲኖረው ከማስቻሉ ባለፈ ሃገራዊ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው ብለዋል። እናቶች በማይመች ሁኔታ ውስጥም ቢሆኑ ለልጆቻቸው የጡት ወተትን መስጠት ማቋረጥ እንደሌለባቸው ለእናቶቹ አስገንዝበው አባቶች፣ የቤተሰብ አባላትና ማህበረሰቡም ለሚያጠቡ እናቶች ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


በስነስርዓቱ የክልሉ እና የአጋር ድርጅት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ሁለት እናቶች ጡት በማጥባት ዙሪያ ተሞክሯቸውን አጋርተው ለተሰበሰቡት እናቶች እስከ ስድስት ወር የእናት ጡት ብቻ የማጥባት ጥቅምን አስረድተዋል። 


የጡት ማጥባት ሳምንት በኮቪድ ወረርሽኝ፣ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ወቅት ለጡት ማጥባት ምቹ አከባቢና ሁኔታዎችን በመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ መንግስት፣ የግል ተቋማትና አጋር ድርጅቶች እንዲሁም ማህበረሰቡ ጡት ማጥባትን ለመጠበቅ፣ ለማስተዋወቅ እና ለመደገፍ እንዲነሳሳ ታሳቢ ተደርጎ ከሃምሌ 25 እስከ ነሃሴ 1 እየተከበረ ይገኛል።