የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ሚና ለነበራቸው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ባለሙያዎች የምስጋና መርሀግብር ተካሄደ።

  • Time to read less than 1 minute
St Paul

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ በተዘጋጀዉ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ባደረጉት ንግግር በሀገራችን ባለፉት ጊዜያት በተከሰቱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና ጦርነት በቀዳሚነት ምላሽ በመስጠት ላበረከቱት አስተዋጽዖ አመስግነዋል። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ አመራሮች እና ሰራተኞች በዛ አስቸጋሪ ወቅት ዋጋ ከፍለው ላሳዩት ርብርብ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ እውቅና እና ምስጋና ያቀርባል ብለዋል።


በዚያ ወረርሽኝ ወቅት የሆስፒታሉ አመራሮች እና ሰራተኞች ቅድሚያ ተነሳሽነት በማሳደር በሚሊኒየም የኮቪድ ማእከል መስዋትነት በመክፈል ጭምር ለሰሩት ስራ እና በሌሎች ክልሎችም ማእከላቱ እንዲስፋፉ በማገዝ ላበረከታችሁት አስተዋጽዎ ምስጋና ይገባችዃል ያሉት ዶክተር ሊያ ትልቅ ስራ እና ሀላፊነትም መወጣት የሚችል አቅም እንዳለን የተገነዘብንበትና የኮራንበት ስራም ነው ብለዋል።


ዶ/ር ወንድማገኝ ገዛኧኝ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ፕሮቮስት በበኩላቸው እንደገለጹት የሆስፒታሉ እና የኮሌጁ ሰራተኞች በወቅቱ ለህይወታቸው ሳይሳሱ ወረርሽኙን ለመቀልበስና ታማሚዎች እንዲያገግሙ ለማገዝ በቁርጠኝነት ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰው ህይወታቸውን ያጡ ባለሙያዎች በመኖራቸውንና ለሁሉም አክብሮትና ምስጋና ማቅረብ ይገባል ብለዋል።


የሕክምና ባለሙያዎች በኮቪድ 19 መከላከል ውስጥ በነበራቸው ቁልፍ ሚና ህይወታቸውን ላጡ የህሊና ጸሎት ተደርጓል።


በዕለቱም ባለፋት ሁለት አመታት ውስጥ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለአደጋ እና ምላሽ ልዩ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷል።


ከዚሁ ጋር በተያያዘም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ባሳለፈው የሰባ አምስት ዓመታት የስኬት ጉዞ መከበር የጀመረ ሲሆን ይህን አስመልክቶም የጤና ሚኒስትር  ዶክተር ሊያ ታደሰ ትምህርትን እና የህክምና አገልግሎት በጥምረት በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። ይህም እንደ ሀገር ታላቅ ኩራት እንደሆነ ገልጸው በቀጣይም ለበለጠ ሀላፊነት መዘጋጀት እንደሚገባ አስረድተዋል።