የቤተሠብ እቅድ አገልግሎትን ለማስፋፋት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የድርሻቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡ ገለፁ። 

  • Time to read less than 1 minute
House of Representatives

ይህ የተገለፀው የጤና ሚኒስቴር በቤተሠብ እቅድ አገልግሎት ተደራሽነት፣ ስኬት እና ክፍተት በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረገው የግንዛቤ መስጨበጫ መድረክ ላይ ነው። በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ እንዳሉት የቤተሠብ እቅድ አገልግሎት መስጠት የሴቶች እና ህጻናት ህይወት ለመታደግ ዋነኛው አቅጣጫ መሆኑን ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ጠቅሰው ይህን አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሠጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸዋል።


ባለፉት አመታት በቤተሠብ እቅድ አገልግሎት የተሠሩ ሥራዎች እና የተገኙ መሻሻሎች እንደተጠበቁ ሆነው አሁንም 22 በመቶ የሚሆኑ በለትዳር ሴቶች አገልግሎቱን ለማግኘት ቢፈልጉም ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን የገለጹት ሚኒስትር ድኤታው ይህም በበጀት አመቱ የገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ ምክንያት መሆኑም አስረድተዋል።


ስለሆነም ይህን የበጀት እና ግብአት ክፍተት ለመሙላት የምክር ቤቱ የድርሻውን ሀላፊነት እንዲወጣ የጠየቁ ሲሆን ህብረተሠቡ በቤተሠብ እቅድ አገልግሎት ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት በማረም ትክክለኛ መረጃ ለማስያዝ የሚረዱ ስራዎች እንዲሠሩ ለአባላቱ ጥሪ አቅርበዋል።


የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ክብርት ሎሚ በዶ በበኩላቸው በየአመቱ የሚሞቱ የእናቶችና ወጣት ሴቶች ቁጥር እየቀነሠ ያለ ቢሆንም አሁንም ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከሚያስችሉን እርምጃዎች አንደኛው የሆነውን የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ጨምሮ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለእነዚህ ተጎጂ ማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ አጽንኦት ተሠጥቶ እንዲሠራ ይገባል ያሉ ሲሆን በዚህ ዙርያ ያለውን የበጀትና የግብአት እጥረት እንዲሁም ህብረተሠቡ ውስጥ ያለውን የግንዛቤ ውስንነት ለመቅረፍ ይሰራል ብለዋል። በመሆኑም የምክር ቤቱ አባላት ወደ ወከላቸው ህብረተሠብ ሲሄዱ ይህን ችግር ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን ድጋፍ አድርገው እንዲሠሩ አሳስበዋል።


የአንድ አገር እድገት ከሚለካባቸው ነጥቦች አንዱ የእናቶች እና የህጻናት ጤና ነው ያሉት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት ዘላለም ሲሆኑ ይህን ለማረጋገጥ ባለፋት አመታት የጤና ተቋማት በማስፋፋት፣ የወሊድ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ፣ በጤና ኤክስቴንሸን ፕሮግራም በኩል ሠፊ የማህበረሠብ ንቅናቄ ተፈጥሮ መሠራቱንና በርካታ ስኬቶች ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።


በተለይ የእናቶች ሞት ከ10ሺህ እናቶች 1 ሺህ ይሞቱ ከነበረው 401 ማድረስ መቻሉንና በቀጣይ 5 አመት 279 ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንና እንደሀገር የእናቶች ሞት ቁጥሩን ወደ 140 ዝቅ ለማድረግ ስለሚጠበቅ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠይቅ ዶክተር መሠረት አስረድተዋል። 


በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የ2021 አመታዊ ስኬት ሪፖርት 8.7 ሚሊዮን በላይ ሴቶች የቤተሠብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን 3.2 ሚሊዮን በላይ ያልታቀደ እርግዝና እና 806 ሺህ ደህንነቱ ያልጠበቀ ጽንስ በማቋረጥ የ10,000 እናቶች ሞት ማስቀረት መቻሉን ዳይሬክተሯ ካቀረቡት መረጃ መረዳት ተችሏል። ይሁን እንጂ አሁንም በዚህ ላይ ሠፊ ክፍተት ያለ መሆኑን አንስተው ይህን ችግር የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ትኩረት ሠጥተው ክትትል እንዲያደርጉና እንዲደግፉ ጠይቀዋል።


የመድረኩ ላይ በተደረገው የውይይት አስተያየት የሠጡ አባላትም የቤተሠብ ምጣኔ አገልግሎትን ለማስፋፋት እና ህብረተሠቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የድርሻቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡ ነው የገለፁት።