እኤአ በ2030 የቲቢ በሽታን ለመግታት ቀጣይነት ባለዉ የልማት ግብ የተያዘዉ ዕቅድን ለማሳካት ተገቢዉን ትኩረት ሳያገኝ የቆየዉ የህጻናትና አፍላ ወጣቶች የቲቢ በሽታ ልይታ፣ ምርመራና ህክምና ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት  ያስፈልጋል።

  • Time to read less than 1 minute
Dr. Lia Tadesse

የኢፌድሪ ጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሎሜ ቶጎ እየተካሄደ ባለዉ 72 ኛው የአፍርካ አህጉር የአለም ጤና ድርጅት መድረክ ላይ እንደገለጹት በኢትዮጵያ በ2015 የጸደቀዉ የህጻናትና አፍላ ወጣቶች የቲቢ በሽታ ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ህጻናትና አፍላ ወጣቶችን ከቲቢ በሽታ የመከላከልና ህክምና ስራ መሻሻሉን ተናግረዋል።  


በኢትዮጵያ በተሰራዉ ስራ በበሽታዉ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር  ቢቀንስም የቲቢ በሸታ እንዲሁም የቲቢ -ኤች አይቪ ጫና አሁንም ከፍተኛ በሆነባቸዉ 30 አገሮች አንዷ መሆኗን ያወሱት ዶ/ር ሊያ፣ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚሰሩ ስራዎች ለቲቢ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑና የተዘነጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።


እኤአ በ2030 የቲቢ በሽታን ለመግታት ቀጣይነት ባለዉ የልማት ግብ  የተያዘወን ዐቅድ ለማሳካት  በተለይም ከሰሃራ በታች ያሉ በቲቢ በሽታ ስርጭት ይበልጥ እየተጎዱ ያሉ እገራት ላይ ትኩረት መስጠትና ማገዝ እንደሚገባ ያሳሰቡት ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ በተለይም ተገቢዉን ትኩረት ሳያገኝ የቆየዉ የህጻናትና አፍላ ወጣቶች የቲቢ በሽታ ልየታ፣ ምርመራና ህክምና ትኩረት ሊያገኝ ይገባል ብለዋል።   


ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ የተያዘዉን የዓለም ጤና አጀንዳ ከግብ ለማድረስ ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ነዉ ያሉት ዶ/ር ሊያ በአጠቃላይ የጤና አገልግሎት ፍትሃዊ ተደራሸነትን በማረጋገጥ ለህጻናትና አፍላ ወጣቶች ትኩረት በመስጠት ከቲቢ በሽታ መከላከልና ሁለንተናዊ ጤንነታቸዉ እንዲጠበቅ ማድረግ አይነተኛ ምሳሌ መሆኑን ተናግረዉ ለዚህ ስራ ስኬት በተለይም የበለጸጉ አገራት፣ አጋር ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የግብኣት እጥረት ያለባቸዉ ድሃ አገራትን እንዲረዱ ጥሪ አቅርበዋል።