የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል በጦርነት ከደረሰበት ጉዳት አገግሞ ሁሉንም አገልግሎቶች በመስጠት ላይ ነው::

  • Time to read less than 1 minute
Boru Meda General Hospital

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ የሆስፒታሉን የተለያዩ የስራ ክፍሎች ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት እንደገለፁት ሆስፒታሉ ከደረሱበት ችግሮች ፈጥኖ በማገገም ለተገልጋዮች የተሟላ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ የሚደነቅ ነው ብለዋል።


የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል በጦርነቱ ወቅት ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው ሆስፒታሎች አንዱ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር አየለ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ የተረባረቡትን ሁሉ አመስግነው በቀጣይም የጤና ሚኒስቴር የጎደሉ የህክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት እየተፈፀሙ ያሉ ግዢዎችን በማፋጠን ሆስፒታሉ የሚጠናከርባቸውን አማራጮች ሁሉ እንደሚያመቻች ተናግረዋል።


በተጨማሪም ሆስፒታሉ ካሉበት የግንባታ ችግሮች መካከል የድንገተኛ ህክምና መስጫ እና የአይን ህክምና ክፍሎች የማስፋፊያ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጀምረውና ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ለማድረግ የጤና ሚኒስቴር የጤና መሰረተ ልማት ዳይሬክቶሬት ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ ዶ/ር አየለ ለሆስፒታሉ አመራሮች ገልፀውላቸዋል።


የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተበጀ እንደገለፁት ከሆነ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ከታህሳስ 2014 ዓም ጀምሮ ለድንገተኛ፣ለወሊድና ለተመላላሽ ቋሚ ታካሚዎች  አገልግሎት መስጠት የጀመረው የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ከዚያ ወዲህ የጎደሉትን እያሟላ ከተመላላሽ ታካሚዎች እስከ ከፍተኛ ቀዶ ህክምና ድረስ እየሰጠና አሰራሩን በየወሩ እያሻሻለ መምጣቱን አስረድተዋል።


ጥገናዎችን ሙሉ በሙሉ በሆስፒታሉ አቅም ማከናወን መቻሉን የገለፁት ስራ አስኪያጁ የጤና ሚኒስቴር ፣የክልሉ ጤና ቢሮ፣ ከፌዴራል የጴጥሮስ እና የአለርት ሆስፒታሎች ፣ ከአማራ ክልል የፍኖተ ሰላምና የየጁቤ ሆስፒታሎች እንዲሁም እንደ ሲቢኤም፣ ሂመሊያ ካታራክት ፕሮጄክት፣ ባለሀብቶችና ግለሰቦች ባደረጉት ርብርብና ድጋፍ ሆስፒታሉ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ አስችለውታል ብለዋል።


በ1947 ዓም የተቋቋመውና በደቡብ ወሎ የሚገኘው የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል 402 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በባለፈው ጦርነት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት ደርሶበት እንደነበር የገለፁት አቶ ሲሳይ በቀጣይም የጎደሉትን አሟልቶ ወደ ነበረበት አሰራር እንዲመለስ የሁሉም ድጋፍና ክትትል እንዳይቋረጥ ጠይቀዋል።