ጤና ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ከረዩ ሰፈር ሶስት የአቅመ ደካማ ቤቶችን ሰርቶ አስረከበ።

  • Time to read less than 1 minute
handed over three houses

ጤና ሚኒስቴር በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ከቤት እድሳት በተጨማሪ የአረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ፣ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ፣ ነፃ የህክምና አገልግሎት፣ የደም ልገሳና ማዕድ ማጋራት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎችም ክልሎች ማከናወኑን የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰን በመወከል አቶ እስክንድር ላቀው የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተናግረዋል።


በዘንድሮው ዓመት የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ጤና ሚኒሰቴር ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራ ሲሆን በተለይም ድጋፍ የሚሹ ቤተሰቦች ቤቶችን ከማደስ ጋር ተያይዞ ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ በጋምቤላ ከተማም የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በእለቱም ቤት ለታደሰላቸው አቅመ ደካማ ግለሰቦች የቁልፍ ርክክብ አድርገዋል።


ቤቱን የተረከቡት ቤተሰቦችም ከእድሳቱ በፊት በተለይም በክረምቱ ወራት ዝናብ ቤታቸው ውስጥ ያንጠባጥብ ስለነበር ተኝቶ ለማደር አስቸጋሪ እንደነበር ተናግረዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አመስግነዋል።


ከዚህ ቀደም ጤና ሚኒስቴር በክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ መርሐ ግብር  ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተጨማሪ በተለያዩ ክልሎች ከ16 በላይ የአባወራዎችና እማወራዎች የቤቶች እድሳት መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።