ሁለተኛው የአለም አቀፍ መድሃኒት አቅራቢዎች ኮንፍረንስ ተካሄደ 

  • Time to read less than 1 minute
group picture

ኮንፍረንሱ የተካሄደው በኢትዮጵያ የሚታየውን የመድሃኒት አቅርቦት ውስንንት ለመሙላት እንዲቻል መድሃኒት አምራች እና አቅራቢዎችን ለመሳብ ታስቦ መሆኑን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልካዲር ገልገሎ ገልጸዋል፡፡ 


ዶ/ር አብዱልካዲር በንግግራቸው እንዳወሱት መድሃኒት አቅርቦት የባለድርሻ አካላት እና የካፒታል ስብጥር የሚጠይቅ በመሆኑ ከአቅራቢዎች ጋር ስትራተጂክ ፓርትነርሺፕ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።


መድሃኒት አቅርቦት በአለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን የተናገሩት የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሄራን ገርባ ሲሆኑ፤ ኮቪድ 19 የመድሃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ችግር መፍጠሩን ተናግረው ኤጀንሲያቸው የመድሃኒት ጥራት ቁጥጥር እና ደህንነት ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰራ መሆኑን እና አገልግሎቱን ለማሻሻል የዲጂታላይዜሽን ስራ በመስራት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡ 


የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል  በሁለተኛው የጤናው ዘርፍ ትርንስፎርሜሽን እቅድ ትኩረት ተሰጥቶት እየተስራ እንደሆነ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ የአርማወር ሀንሰ የምርምር ኢኒስቲቲዩት ዳይሬክተር የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰን በመወከል ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል፡፡ 


የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢዎች አገልግሎት ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ቁልፍ ሚና ያለው ሲሆን በሽታ መከላከል እና ለህክምና የሚሆን መድሃኒት በማቅረብ የማይተካ አስተዋጾ እንዳለው ፕ/ር አፈወርቅ አስታውሰዋል፡፡ ጤና ሚኒስቴር ለአለም አቀፍ እና ሃገር ውስጥ መድሃኒት አቅራቢዎች የሚየደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።


በኮንፍረንሱ ላይ ብሄራዊ የመድሃኒት አቅርቦት ዘርፍ ያለበትን ጠቅላላ ሁኔታ እና የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ኤጀንሲ የምዝገባ መመሪያዎች እና ደንቦች እንዲሁም የ2021 – 2022 የመድሃኒት አቅራቢዎች አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ በኮንፍረንሱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡


ባለፉት ሁለት አመታት በመድሃኒት አቅርቦት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ድርጅቶችም የእውቅና  ሽልማት ተበርክቷል፡፡