በጤና ኤክስቴንሽን መርሃ-ግብር ትግበራ የአጋር ድርጅቶች ሚና ውጤታማ ነበር

  • Time to read less than 1 minute
Health Extension

በጤና ኤክስቴንሽን መርሃ-ግብር ትግበራ በርካታ የጤና አገልግሎቶች ማህበረሰቡን ተደራሸ ለማድረግ የአጋር ድርጅቶች ሚና ውጤታማ እንደነበር እና እንደ ሃገር አመርቂ የጤና ውጤቶች የተመዘገበበት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ 


በፕሮግራሙ  ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ድጉማ እንደገለጹት የጤና ስርዓታችን በተለይም የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎትና የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነበት የጄ ኤስ አይ/ኤል10ኬ 10 ኪሎ ሜትር/JSI L10K 10K/ ባለፉት 14 ዓመታት የነበረው አገልግሎት ውጤታማ እንደነበር አንስተው ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት በመስራት ለተገኘው ውጤትና ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው። በቀጣይም ይህ ፕሮጅክት ቀጣይነት እንዲኖረው ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት በትብብር ውጤታማ ስራ ለመስራት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡   


የJSI ፕሮጅክት ስራ አስኪያጅ ማርጋሬት ክሮቲ በበኩላቸው እንደተናገሩት ፕሮጅክቱ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎትን ለማጠናከር እና ከ17 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ጠቃሚ እንደነበር ጠቁመው በተለይ በሥነ ተዋልዶ፣ በእናቶችና ሕጻናት ጤና፣ እንዲሁም በአፍላ ወጣቶች የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ውጤታማ ሥራ እንደተሰራ ተናግረዋል፡፡


ሃላፊዋ አክለውም እ.ኤ.አ ከ2008-2022 በተካሄደው 14 ፕሮጀክት የተሻሻለ የስነ ተዋልዶ፣ የእናቶች፣ የጨቅላ ህጻናት እና ታዳጊዎች ጤና አገልግሎትን ከ5,000 በሚበልጡ ቀበሌዎች እና 240 ወረዳዎች በአራት ክልሎች ላይ ውጤታማ ስራ እንደተሰራ ጠቁመው በተለይ ማህበረሰቡ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ከ10,000 በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ጋር እና ከ100,000 የሚሆኑ የሴት የልማት ሰራዊት እንዲሁም የማህበረሰብ ጤና በጎ ፈቃደኞች ጋር በማስተሳሰር ፕሮጅክቱ የተሳከ ስራ እንደሰራ አብራርተው ለጤና ሚኒስቴርና ስራውን በጋራ ሲሰሩ ለነበሩ አጋር አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ 


በፕሮግራሙ ላይ የጤና ኤክስቴንሽን ተወካዮች ፣የጤና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ የጄኤስአይ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች አካላት ተገኝቷል።