በፌደራል ጤና ሚኒስቴር እና ግብርና ሚኒስቴር የሚመራ የዓለም ጤና ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅትን ያካተተ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በድርቅ የተጎዳዉን የሱማሌ ክልል ሸበሌ ዞንን ጎብኝቷል።

  • Time to read less than 1 minute
Somali

የጎዴ አጠቃላይ ሆስፒታል የምግብ እጥረት ህክምና መስጫ ማዕከልን፣ ፈጣን ምላሽ ህክምና አሰጣጥን እንዲሁም በጎዴ ወረዳ የክትባት፣ የስነ ምግብ፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ድጋፍ፣ የእንስሳት ምገባ ድጋፍ አገልግሎት ለማህበረሰቡ በፌደራል በክልልና በአጋር ድርጅቶች ቅንጅት እየተሰጠ የሚገኝበትን ሁኔታም ተመልክቷል።


ከጉብኝቱ በተጨማሪም ቡድኑ ከክልሉ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሙስጤፌ መሃመድ እና ከሌሎች የክልሉ ሃላፊዎች ጋር በድርቅ የተጎዱ ቦታዎችን ምላሽ አሰጣጥና ድጋፍ ዙሪያ ውይይት አድርጓል። 


ቡድኑ በድርቁ የተጎዱ እና የጤና ጉዳት የደረሰባቸዉን ዜጎች ለማከም፤ እንዲሁም የተጎጂ ጨቅላ ህጻናትን ልዩ የምግብ ፍላጎት ለመደገፍ የሚዉሉ ከአለም ጤና ድርጅት የተገኙ ሃምሳ ሜትሪክ ቶን የድንገተኛ ህክምና ቁሳቁስ ድጋፍም የተበረከተ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸዉን ዜጎች ለመደገፍ እና ሊከሰት የሚችለዉን ወረርሽኝ ለመከላከል/ለመቆጣጠር የፌደራል መንግስት እና ተመድ አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አመልክቷል።


ቡድኑ የጤና ሚንስቴር ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የግብርና ሚንስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ እና ዶ/ር መለስ መኮንን የአለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶ/ር ቡሬማ ሃማሳምቦ፣ የምግብና የእርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶ/ር ፋጡማ ሰዒድ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህን አካቷል።