የግሎባል ፈንድ አፈጻጸም እና ትግበራ በተመለከተ ከሲውዘርላንድ ከመጡ ከፍተኛ የተቋሙ አባላት ጋር ውይይት ተደረገ

  • Time to read less than 1 minute
Global Fund

ሲውዘርላንድ ጄኔቭ ከሚገኘዉ የግሎባል ፈንድ ዋና መስሪያቤት የመጣው ከፍተኛ የአመራርና የባለሙያዎች ቡድን ጋር በደተረገው ውይይት ላይ የሃይ ኢምፓክት አፍሪካ ሄድ ኦፍ ዲፓርትመንት እና የዴሊጌሽኑ መሪ የሆኑት ሊንደን ሞሪሰን እንዳሉት ኢትዮጵያ የተላያዩ ችግሮች ያጋጠሟት ቢሆንም በግሎባል ፈንድ ድጋፍ የሚደረግላቸዉ የጤና ፕሮግራሞች አፈጻጸም ግን ጥሩ በመሆኑ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡


በግሎባል ፈንድ ስር የሚከወኑ ፕሮግራሞችን እና የኮቪድ መከላከል ስራዎች መልካም ውጤት ያስገኙ መሆናቸው የገለጹት የጤና ሚኒስቴር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ናቸው፡፡ የውጭ ምንዛሬ አለመረጋጋት እና ግጭት የግሎባል ፈንድ አፈጻፀም እና ትግበራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች እንደሆኑ ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል፡፡ ያጋጠሙ የአቅርቦት ችግሮችን መቅረፍ ይገባል ያሉት ዶ/ር ሊያ፣ በግሎባል ፈንድ አፈጻጸም እና ትግበራ ላይ አጋር ድርጅቶች ያደረጉትን ተሳትፎ አድንቀዋል፡፡

 
ምንም እንኳ እንደ ኮቪድ ያሉ ችግሮች ያጋጠሙ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ትስስር እና አጋርነት መፍጠር መቻሉን የገለጹት የሃይ ኢምፓክት አፍሪካ ሲኒየር ፖርትፎሊዮ ማኔጀር የሆኑት ጆርጅ ሳክቫርሊድዝ ሲሆኑ በተለይም የባለፉት ሁለት አመታት ትግበራ አመርቂ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ 


የኑሮ ውድነት እና የውጭ ምንዛሬ አለመረጋጋትን ለመቅረፍ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር እንደሚሰሩ ሲኒየር ማኔጀሩ የገለጹ ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመው የአቅርቦት መስተጓጓል ለአፈጻጸም ትልቅ ችግር ነው ብለዋል፡፡
የግሎባል ፈንድ በቲቢ፣ ኤች አይ ቪ፣ ማሌሪያ እና ኮቪድ ላይ የሚያደረገው እገዛ ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ ግምገማ ያቀረቡት ዶ/ር አበራ በቀለ እንዳሉት የኢትዮጵያ ሃገር አቀፍ ትግበራ በአጠቃላይ ሲታይ መልካም ነው ብለዋል፡፡


የላብራቶሪ ሲስተም በሃገር አቀፍ ደረጃ ማጠናከር እና የጥራት ፍተሻ ስራዎችን ማጠናከር እና የጤና ማኔጅመንት መረጃ ስርአትን ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራዎችም እንደተሰሩ ዶ/ር አበራ ገልጸዋል፡፡
የኮቪድ ወረርሽኝ አሁን ላይ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም የክትባት ስርጭት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑ አበረታች ነው ያሉት ዶ/ር አበራ፣ የግብአቶች ስርጭት እና የግዢ መስተጓጓል ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንደነበሩ አስተውሰዋል፡፡


የግሎባል ፈንድ ሪፖርት በጤና ጥበቃ የትግበራ እቅድ ውስጥ እንደሚካተት የገለጹት የጤና ሚኒስቴር ዲኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ሲሆኑ፣ የግሎባል ፈንድ ትግበራ ጤና ሚኒስቴር ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ክንውኖች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ኮቪድ፣ ድርቅ እና ሌሎች በሃገር አቀፍ ደረጃ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ጤና ሚኒስቴር እንደሚሰራ ዶ/ር ደረጀ ተናግረዋል፡፡