በኢትዮጵያና በአጎራባች ሀገራት የጤና ስርዓትን  ለማጠናከር የሚያግዙ ስምምነቶችና እርዳታዎች ተደረጉ፡፡

  • Time to read less than 1 minute
Agreements

የሀገራችን የጤና ስርዓትን በማጠናከር የሀገር ውስጥና ድንበር ተሻጋሪ የጤና በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የበለጠ ተግቶ መስራት እንዲቻል በዛሬው እለት በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአውሮፓ ህብረት ድጋፍና በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ)እንዲሁም በዩኖፕስ አስተባባሪነት የኢትዮጵያንና የአጎራባች ሀገራት የጤና ስርዓትና የኮቪድ-19 ምላሽን ለመደገፍ ለኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር በተደረገው ልዩ ልዩ የጤና አምቡላንሶችና ቁሳቁሶች ርክክብ እና የመግባቢያ ሠነድ ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት የተሻለ ጤናን መኖር የሚቻለው የተሻለ የጤና ሥርዓት ሲገነባ እንደሆነ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡


የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የኮቪድ-19ና ሌሎች ድንገተኛ ወርረሽኞች የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመቀነስና ለመከላከል ይቻል ዘንዳ በሀገር ውስጥና በድንበር አካባቢ ልዩ ልዩ የቅኝትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን እንዲሁም ተገቢውን የጤና ግንዛቤ በማስጨበጥ ተጋዦች በድንበር አካባቢ የሚገኙ ተመላላሽ የህብረተሰብ ክፍሎች ራስቸውን እና ህብረተሰቡን ከልዩ ልዩ በሽታዎች እንዲጠብቁ እየተሰራ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡


ክብርት ዶ/ር ሊያ አያይዘውም በድንበር አካባቢ የጤና ስርዓትን ለማጠናከር የሚሰሩ ስራዎች ለቀጠናዊ ትስስር እና ድንበር ተሻጋሪ የሆነ የጤና ምርምር ቅኝትን ከማጠናከር እና ከማጎልበት አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተው የፋይናንሰ እርዳታ በኢጋድ በኩል ላደረገው ለአውሮፓ ህብረት እና ለሌሎች  አጋር አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡


ክቡር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ዋና ፀሀፊ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት በሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት የጤና ስርዓታቸውን ለመደገፍ እና ለማጠናከር ተግቶ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ 


በቀጣይም የሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት ህዝቦችን ተጠቃሚነት ትስስርና ትብብርን የሚያጎሉ እርዳታዎችና እገዛዎች እንደሚደረጉ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ አጋጣሚም ዘወትር አጋር የሆነውን አውሮፓ ህብረትን አመስግነዋል፡፡


በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር ሮናልድ ኮቤ በከፍተኛ ትኩረት ለሚደረገው የክትባት ፕሮግራም አድናቆታቸውን በመግለጽ ድጋፉ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡


በኢትዮጵያ የዩኖፕስ ዳይሬክተር እና በአፍሪካ ህብረት ተጠሪ ወ/ሮ ወርቅነሽ መኮንን በበኩላቸው ስምምነቱንና እርዳታውን አመስግነው የወደፊት ትብብሮች እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡


የኢትዮጵያን የጤና ስርዓት ለማገዝ እንዲረዳ ሶስት አምፑላንሶችና አንድ እጅግ ዘመናዊ የሆነ ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ እንዲሁም ሌሎች የጤና ቁሳቁሶች ርክክብ ሥነ-ሥርዓት የተከናወነ ሲሆን በኢትዮጵያ እና በጁቡቲ መንግስታት መካከል በድንበር ተሻጋሪ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው ማዕከል ያደረገ ክትባት ዙርያ በኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር እና በጁቡቲ የጤና ሚኒስትር እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) መካከል የሶስትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ፊርማ ስነስርዓት ተከናውኗል፡፡


በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ከጤና ሚኒስቴር፤ ከጎንደር ዮኒቨርሲቲ እና ከጅጅጋ ዮኒቨርሲቲ ጋር በህብረተሰብ የጤና ግንዛቤ ማሻሻያ ስራና ምርምር ላይ አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ሥነ-ሥርዓትም የተከናወነ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት የጤና ሚኒስቴር እና በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር በምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ስራና ምርምር ላይ የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ፊርማ ሥነ-ሥርዓትና የመግባቢያ ስምምነት ተግባራዊ የሚሆንበት የ1.7 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር በላይ በኢጋድ በኩል ለኢትዮጵያ ተደርጓል፡፡

ይህ በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አስተባባሪነት የሚከናወኑ የጤና እና ጤና ነክ ስራዎች በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር በማጎልበት በለጋሽ ድርጅቶች ደጋፊነት በድንበርና ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎች ቁጥጥር አማካኝነት የጤናውን ዘርፍ ማጠናከር ተቀዳሚ አላማው አድርጎ የተነሳ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ምላሽ እንደሚሰጥ ይገመታል።