"በግሎባል ፈንድ የሚተገበሩ ፕሮግራሞች ውጤት ተኮር በመሆናቸው ሁሉም አካል በትኩረት ሊሰራባቸው ይገባል።" የጤና ሚኒስትር ዴኤታ - ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ

  • Time to read less than 1 minute
Dr. Dereje Duguma

ግሎባል ፉንድ ግራንት ፕሮግራም ትግበራ ሂደቶችን የመገምገም እና እስካሁን በተያዙ እቅዶች አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ግምገማ  ዛሬ በጤና ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ 


የግምገማ መድረኩ በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የተመራ ሲሆን ትኩረቱንም እስካሁን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከግሎባል ፈንድ በተገኝው የፋይናንስ ድጋፍ በጤናው ዘረፍ የተከናወኑ ዝርዝር ስራዎች ቀድሞ ከታቀደው እቅድ አኳያ አሁናዊ ደረጃው ምን እንደሚመስል እና የእቅድ አተገባበሩ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተገመገመበት ነው።


የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በግምገማ መድረኩ እንደተናገሩት በግሎባል ፈንድ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ውጤት ተኮር በመሆናቸው ሁሉም አካል በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባ  አንስተዋል፡፡ 


በፕሮጀክት ትግበራውም ወቅት የታዩ መልካም ተምከሮዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል  እንደሚገባ እና የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ተጠባቂውን ውጤት ለማስመዝገብ መስራት እንደሚያፈልግ ተናግረዋል፡፡


በግምገማ መድረኩም የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት እንዲሁም የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን እና የጤና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች  የተሳተፉበት ነው፡፡ ተሳታፊዎችም የታቀዱ እቅዶችን ከማስፈጸም እና ከመከታተል አንጻር  ከዚህ ቀደም የሰሩዋቸውን ስራዎች እና ያሉበትን ደረጃ አቅርበዋል፡፡


በመጨረሻም በግሎባል ፈንድ የሚተገበሩ ፕሮግራም በታቀደው መሰረት ለማጠናቀቅ እንዲቻል እና አስፈላጊውን ውጤት ለማስመዝገብ እንዲቻል ሁሉም አካል በትኩረት እና ያለ አንዳች መዘናጋት በተያዘው ግዜ ያቀድናቸውን ስራዎች ለማሳካት እንድንችል በትብብር ሊሰራ ይገባል ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በታዩ ክፍተቶች ላይ አስፈላጊው እርምት ሊወሰድ እንደሚገባ የስራ መመሪያ ሰተዋል፡፡


ግሎባል ፉንድ የወባ በሽታ፣ ኤችአይቪኤድስ፣ ኮቪድ-19 እንዲሁም የጤና ስርአት ማጠናከር ላይ የሚተገበር ፕሮግራም ሲሆን ከግሎባል ፈንድ በተገኝው የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን ያካትታል፡፡