በአማራ እና አፋር ክልሎች ጉዳት ለደረሰባቸው የሆስፒታል ላብራቶሪዎችን መልሶ ለማቋቋም የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ 

  • Time to read less than 1 minute
donation

6.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የላብራቶሪ ህክምና ቁሳቁስ ድጋፍን ያደረገው የኦሃዮ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ ሲሆን በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው የህክምና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚውል መሆኑ ተገልጿል፡፡ 


የጤናው ዘርፍ በጦርነቱ ከፍተኛ ውድመት ያሰተናገደ ዘርፍ መሆኑን የገለጹት የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴዔታ ዶ/ር አየለ ተሸመ፤ የተደረገው ድጋፍ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 


የላብራቶሪ ህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ተቋማት የተሟላ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚደገፍ መሆኑን በመግለጽ ስለተደረገው ድጋፍ በጤና ሚኒስቴር፣ ድጋፍ በተደረገላቸው ተቋማት እና በተቋማቱ አገልግሎት በሚያገኙ ማህበረሰቦች ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ 


የላብራቶሪ ቁሳቁሶቹን ድጋፍ ያደረገው ኦሃዮ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ ከጤና ሚኒስቴር እና ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር ላለፉት 10 አመታት ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት የኦሃዮ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ ቴክኒካል ዳይሬክተር  ዶ/ር ኤባ አባተ ናቸው፡፡ 


ኦሃዮ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ በ18 ሚሊዮን ዶላር በጀት የ5 አመት ፕሮጀክት በመተግበር ላይ እንደሚገኝ እና ከሚሰራቸው ስራዎች በተጨማሪ በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋት ድጋፍ ማድረጉ ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ የስልጠና እና የህክምና ግብአት ድጋፉ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶ/ር ኤባ አክለው ገልጸዋል፡፡  


ድጋፉ እንዲደረግ የማስተባበር ስራ የሰራው ሲ.ዲ.ሲ ሲሆን የሲ.ዲ.ሲ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶ/ር ካሮላይን ራየን ጥራት ያለው የላብራቶሪ ህክምና ቁሳቁስ መኖር ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተናግሮ ሲ.ዲ.ሲ ወደፊትም ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኦሃዮ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል፡፡ 


የላብራቶሪ ህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ተቋማት አጣዬ ሆስፒታል፣ ኮምቦልቻ ሆስፒታል፣ ሃይቅ ሆስፒታል፣ ወልድያ ሆስፒታል፣ እና ከለዋን ሆስፒታሎች ሲሆኑ የሰሜን ወሎ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት የቢሮ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡ 


ጉዳት ለደረሰባቸው ተቋማቱ የተደረገው የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማይክሮስኮፕ፣ ሴንተርፊዩጅ፣ ኢንኩቤተር፣ ፍሪጅ፣ ፒ.ኤስ፣ እና ስታብላይዘር ያሉ የላብራቶሪ ግብአቶችን ጨምሮ የህክምና ንጽና መጠበቂያዎችን ያካተተ ነው፡፡