በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ምግብን መሠረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ ይፋ ተደረገ 

  • Time to read less than 1 minute
Nutrition

የጤና ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር እና አጋር አካላት በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት በጋራ ያዘጋጁት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ምግብን መሠረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ (Food-Based Dietary Guidelines (FBDG's) በዛሬው ዕለት ይፋ ሆኗል። 


በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሀገራችን ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ የ2019 ጥናቱ እንደሚያመለክተው 54 በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች እንዲመገቡ ከሚመከረው ሰባት የምግብ ምድቦች ውስጥ ከአራት በታች የሚመገቡ ሲሆን  በተለይም ህፃናትና ሴቶች አነስተኛ ቁጥር ያለው የምግብ ምድብ ስብጥር እንደሚመገቡ ይህም ለመቀንጨርና ሌሎች የጤና እክሎች መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ጥናቱ እንደሚያሳይ ገልፀው ይህም የአመጋገብ ሁኔታን ለማሻሻል የአመጋገብ መስፈርቶችን ያማከለ እና በንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምግቦችን ያካተተ የአመጋገብ ስርዓትን ለመተግበር መመሪያው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።


በመድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ሀገሪቱ ያስቀመጠቸውን የምግብ ምርታማነት ለማሻሻል ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ-ግብር በየአመቱ እንዲስፋፋ ለማድረግ በተያዘው ዓመት ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የመርሀ-ግብሩ ተጠቃሚ እንደሆኑ ተናግረው በቀጣይም ምግብን መሠረት ያደረገ የስነ አመጋገብ ስርዓትን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ሀገር አቀፍ የአመጋገብ ባህልን የማሻሻል ተልዕኮውን ለማሳካት የተለያዩ ስራዎች እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ 


የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው ግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለሀገር ዕድገት መሰረት ቁልፍ የሆነውን ማህበረሰብ ማሳደግ እንደሆነ በመገንዘብ ባለፉት አመታት ስርዓተ-ምግብን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው መመሪያው የጋራ ሀላፊነትን በመውሰድ ስራን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል አሰራር ይዞ የቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 


በሀገራችን ኢትዮጵያ ይህን የመጀመሪያ የአመጋገብ መመሪያ ስታዘጋጅ በአፍሪካ ከስምንቱ የአመጋገብ መመሪያ ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ የሚያደጋት መሆኑን ተገልጿል።