‘የጤና መረጃ ሥርዓትን ለማሻሻል አጋርነት እና ትብብርን ማጠናከር’ በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና መረጃ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከበረ ነው።

  • Time to read less than 1 minute
DATA WEEK

በበዓሉ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትር ፅ/ቤት ሀላፊ ዶ/ር ሩት ንጋቱ በጤናው ሴክቴር የሚታየውን የመረጃ ጥራት ተደራሽነት እና አጠቃቀም ጉድለት በመቅረፍ የጤና አግልግሎት ዘርፉን ማሻሻል እና ተደራሽ ማድረግ ዋና የትኩረት አቅጣጫው መሆኑንን ገልፀው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትግበራ ዘመን የጤና መረጃ ጥራትን ለማሻሻል የመረጃ አጠቃቀም ባህሪን ለማጎልበት እና መረጃን ዋቢ ያደረገ የውሳኔ አስጣጥ አስራርን ለማስረፅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በዛሬው ቀን በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ የጤና ኢኒስቲትዩት የተዘጋጁ ‘ሀገር አቀፍ የመረጃ ተደራሽነትና ማጋራት መመሪያ’ (National Health Data Access and Sharing Guideline) እና ‘ሀገራዊ እና ክልላዊ የጤና ፍኖተ ካርታ (National and Regional Health Atlas) በይፋ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን የጤና መረጃ ተደራሽነትና በመረጃ ቅብብሎሽ እና አጠቃቀም ላይ ያሉ መሠረታዊ ክፍተቶችን ለመፍታት ያግዛል።

ጤና ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት፤ ከክልልና ከተማ አስተደዳደር ጤና ቢሮዎች እና እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዘመናዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት የተሻሻለ የጤና አግልግሎት ፍትሀዊነት እና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሳምንቱ የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ በተዋረድ እስከ ጤና ተቋማት ድረስ የጤና መረጃ ጥራት ተደራሽነትን አጠቃቀምን በሚያጉላ መልኩ ከመጋቢት 5-9/2014 ዓ.ም በተለያዩ ኩነቶች እንደሚከበር በመድረኩ ላይ ተገልጧል፡፡