በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በተደረገ ከሀያ አራት ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአይን ሕክምና ድጋፍ ከሶስት ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የአይን ቀዶ ጥገና ህክምና መስጠት መቻሉ ተገለጸ፡፡

  • Time to read less than 1 minute
የአይን ሞራ ግርዶሽ  የነጻ ህክምና

የጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት በአይን ህክምና ዙሪያ ከሚሰሩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር ከሃያ አራት ሚሊየን ብር በላይ  ድጋፍ በማሰባሰብና የህክምና ባለሙያቸው ድጋፍን በማቀናጀት በአፋር እና በአማራ ክልሎች  በጦርነቱ ምክንያት ህክምና ሳያገኙ የቆዩ ከሶስት ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የአይን ሞራ ግርዶሽ  የነጻ ህክምና መስጠት መቻሉን  እና የህክምና ተቋማቱም በመደበኛ አገልግሎታቸው ህክምናውን መስጠት የሚያስችላቸው ስራ መከናወኑን  የጤና ሚኒስትር የበሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት ሰሎሞን  አስታወቁ፡፡

ዳይሬክተሯ  እንደተናገሩት   በዘመቻው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዲሆን የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን  እና  የዓይን ጤና ክብካቤ ሥራ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆንና ለዘመቻው መሳካት የመድኃኒት፣ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ላደረጉ የመንግስት ተቋማት አጋር ድርጅቶች የግል የአይን ጤና ክሊኒኮች ማህበራትና ግለሰቦች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የአይን ጤና ፕሮግራም አስተባባሪ ወ/ሮ መንበረ በላይ  በበኩላቸው በአማራና በአፋር ክልል ጉዳት የደረሰባቸውን የዓይን ጤና ተቋማት በጊዜያዊነት ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግና አብልጦ ለመገንባት በታቀደው መሰረት የደሴ ሆስፒታል፤የወልዲያ ሆስፒታል፤የዱብቲ ሆስፒታል፤የሞሃመድ አኪል ሆስፒታል  የአይን ህክምና መሳሪያ ፣ግብአትና መድሀኒት ድጋፍ  እንደተደረገላቸው አስተባበሪዋ ተናግረዋል፡፡ አስተባባሪዋ አክለው እንደተናገሩት ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ለሰባት ቀናት  የዓይን ሞራ ግርዶሽ ስርጭት ከፍተኛ በሆነባቸው አከባቢዎች የባለሙያዎች ቡድን በማደራጀት የዘመቻ ህክምናው እየተሰጠ  መሆኑን ተናግረው በሽታው የማህበረሰብ ጤና ችግር ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ሁሉን አቀፍ የህክምናና የመከላከል ስራ  ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

በአማራ ክልል የቦሩ ሜዳ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተበጀ በበኩላቸው በቦሩ ሜዳ ሆስፒታል  በ 3 ቀናት ብቻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት የሚከሰት የዓይነ ስውርነት ችግር ያለባቸው ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን  ተናግረው ይህን ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል

በአጠቃላይ በአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ዘመቻው በአማራ ክልል  በደሴ ሆስፒታል ለ826 ታካሚዎች በዳይሬክት ኤድ  ድጋፍ እንዲሁም በቦሩ ሜዳ ሆስፒታል 1000  ታካሚዎች ደግሞ በሂማሊያ ካታራክት ፕሮጀክት ድጋፍ በአፍር ክልል ከአንድ ሺህ በላይ በአጠቃላይ ከስስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የዓይን ብርሃናቸውን መመለስ መቻሉ  ታዉቋል፡፡

በቀሩት ቀናትም  የማህበረሰብ አቀፍ የዓይን ጤና ሁኔታ  ልየታና የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ህክምና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው  ድጋፉን ላደረጉ የመንግስት ተቋማት አጋር ድርጅቶች የግል የአይን ጤና ክሊኒኮች ማህበራትና ግለሰቦች የእውቅናና የምስጋና ሰርተፍኬት ተበርክቷል።

በሀገራችንም እስከ 50 በመቶ የሚሆነው የአይነ ስውርነት ምክንያት የአይን ሞራ /ካታራክት/ መሆኑን  መረጃዎች ያሳያሉ ፡፡