የሚሊኒየም ኮቪድ ህክምና እና ድንገተኛ ምላሽ ማዕከል የምስጋና እና የማስረከብ ፕሮግራም ተከናወነ

  • Time to read less than 1 minute
የሚሊኒየም ኮቪድ ህክምና እና ድንገተኛ ምላሽ ማዕከል

የጤና ሚኒስቴር ላለፉት ሁለት ዓመታት የኮቪድ የህክምና እና የድንገተኛ ምላሽ ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል የቆየውን አዲስ ፓርክ /የሚሊኒየም አዳራሽ/ ከምስጋና ጋር ለሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አስረከበ።


የጤና ሚኒሰቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ማዕከሉን ለሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባስረከቡበት ወቅት እንደገለፁት ባለፉት ሁለት ዓመታት የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል ብዙ ውጣ ውረዶች ማለፋቸውን ጠቅሰው ዛሬም ኮቪድ እያስከተለ ያለው ችግር ባይቆምም ለዚህ ዕለት በመብቃታችንና የሚሊኒየም የህክምና ማዕከልን መልሰን ማስረከብ በመቻላችን ደስተኞች ነን ብለዋል።


ኮቪድን ለመከላከል በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከሚመራው ብሄራዊ ኮሚቴ ጀምሮ እስከ ማህበረሰቡ ድረስ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉን ያስታወሱት ዶ/ር ሊያ ወረርሽኙ በከፋበት ወቅት ለብሄራዊ ኮሚቴው ቀርቦ ለነበረው አዲስ ፓርክን ለኮቪድ 19 የህክምና ማዕከልነት የመጠቀም ጥያቄ አዲስ ፓርክ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ላሳዩት ቀና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።


በስምንት ሳምንታት ዝግጅት አዳራሾቹን ወደ ሆስፒታልነት በመቀየርና ግብዓቶችን በማሟላት ስራ ተጀምሮ ብዙዎች እንዲፈወሱበት ማድረግ መቻሉን የገለፁት ዶ/ር ሊያ ታደሰ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ ስራውን በኃላፊነት በመረከብና ሌሎችን በማስተባበር ላከናወነው ውጤታማ ስራ አመስግነዋል።


ዛሬ የኮቪድ19  የህክምና እና የድንገተኛ ምላሽ ማዕከሉን ዘግተን ወደነበረበት የምንመልሰው ኮቪድ ስለጠፋ ሳይሆን አገልግሎቱን በሌሎች የጤና ተቋማት ለማቅረብ የምንችልበት አቅም ስለፈጠርንና በመላ ሀገሪቱ የክትባት ሽፋንን በማድረስና የበሽታውን ጉዳት መቀነስ በመቻሉ እንደሆነ ተናግረው በቀጣይም ክትባቱን ያልወሰዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲወስዱና ጥንቃቄያቸውን ሳይዘናጉ እንዲተገብሩ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።


በማዕከሉ የተከናወኑት ተግባራት ለትውልድና ለታራክ እንዲተላለፉ መረጃዎችን በሚገባ ማደራጀት ይገባል ያሉት ዶ/ር ሊያ በማዕከሉ በመሰባሰብ ለታማሚዎች በቅንነት አገልግሎት ለሰጡት ሁሉ ምስጋና አቅርበው የምስክር ወረቀት ለተዘጋጀላቸው አበርክተዋል።


በምስጋና እና በርክክቡ ወቅት ንግግር ያደረጉት የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ ይህ ማዕከል ባለፉት ሁለት ዓመታት ያከናወነው ተግባር የሜድሮክ ባለቤት ሼህ መሀመድ አሊ አላሙዲን ዘወትር ንብረታቸው የህዝብ መሆኑን በሚገባ በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን ገልጸው ተቋሙ ኮቪድን ለመከላከል 120 ሚሊዮን ብር ለአዲስ አበባ መስተዳድር ይህን አደራሽ ለጤና ሚኒስቴር በነፃ እንደሰጠ ሁሉ በቀጣይም ለህዝብ ጥያቄዎች የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።


የህክምና ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ውለታው ጫኔ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በማዕከሉ የቀዶ ህክምና እና የአይሲዩ ክፍሎችን ጨምሮ በአንድ ሺ የህክምና አልጋዎች ከስምንት ሺ በላይ የኮቪድ ታማሚዎች ታክመው እንዲፈወሱ ማድረግ ተችሏል ካሉ በኋላ ለ1633 የቀዶ ህክምና ፈላጊዎች አገልግሎቱ መሰጠቱንና በመላ ሀገሪቱ በኮቪድ ከተያዙት ሰዎች ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በማዕከሉ መታከማቸውን አስታውሰዋል።