በህግ ማስከበር እና በህልውና ዘመቻው አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጤናው ዘርፍ አካላት ምስጋናና እውቅና ተሰጣቸው

  • Time to read less than 1 minute
Gratitude and recognition program

በሃገራችን በተካሄደው በህግ ማስከበር እና በህልውና ዘመቻው ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ጤና ተቋማት፣ ጤና ክብካቤ ባለሙያዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሚኒስቴር በጋራ የተዘጋጀ የምስጋና የእውቅና መርሃ ግብር ተካሄደ፡፡


በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር የጤና ባለሙያዎችና የጤና ክብካቤ ሰራተኞች እንደ ሰው፣ እንደ ኢትዮጵያዊ እና እንደ ሃኪም ሶስት ማንነትን ተላብሳችሁ ለሰራችሁት ታላቅ ገድል ከፍተኛ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል፡፡


ዶ/ር አብይ አህመድ ሶስት ማንነትን ሲያብራሩም  ሰው በመሆናችሁ የወገንን ሃይል ብቻ ሳይሆን የቆሰለን ጠላት ጭምር መስዋዕትነት ሁሉ ከፍላችሁ የሰብአዊነት ሚዛንን ጠብቃችሁ፣ አክማችሁ አድናችኋል፣ ኢትዮጵያዊ ሆናችሁም በታላቅ ጀግንነት አስቦና ተመካክሮ ሰውን መርዳት አዳጋች በሆነበት በዚያ የጦርነት ቀጠና ገብታችሁ የኢትዮጵያዊነትን ጥግ አሳይታችሁናል፤ ሙያዊ ግዴታ እንዳለበት ጤና ባለሙያም ያስተማራችሁን ህዝብ ለመታደግ ግዴታችሁን ተወጥታችኋልና የኢትዮጵያ መንግስት፤ እኔም በግሌ ያለኝን ምስጋና ከታላቅ አክብሮት ጋር አቀርብላችኋለሁ ብለዋል፡፡ 


የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ በበኩላቸው በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ባለፈው አንድ ዓመት በገጠመን ግልጽ የህልውና ፈተና ምክንያት ተገደን ወደ ጦርነት በመግባታችን ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶች ተከስተዋል፤ ይሁን እንጂ የገጠሙንን ፈተናዎች በነበረን አንድነትና ህብረት፣ በነበረን አገራዊና ህዝባዊ ፍቅርና በተለያየ ዘርፍ በተወሰደ ጠንካራ አመራር ችግሮቹ ቢፈትኑንም ከያዝነው ዓላማ ሳያደናቅፉን ብዙዎቹን ተሻግረናቸዋል፤ አሁንም እየተሻገርናቸው ነው ብለዋል፡፡ 


የጤና ሚኒስቴር ጦርነቱ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ግብረ ሃይል በማቋቋም፣ አስፈላጊ መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎችን እንዲሟሉ ቀን ከሌሊት በቅንጅት በመስራት ለመከላከያ ሰራዊቱ ያለውን አብሮነት በተግባር በማሳየት የሚጠበቅበትን ሃገራዊ ምላሽ ለመስጠት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲሰራ እንደቆየ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ አስታውቀዋል፡፡


በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የጤና ተቋማት፣ ጤና ባለሙያዎችና የክብካቤ ሰራተኞች ከፍተኛ ሚና የነበራቸው መሆኑን ጠቅሰው ለመከላከያችን እና ለሌሎች የጸጥታ አካላት ደጀን በመሆን በጦርነቱ የተጎዱትን ወደ ጤና ተቋም በማድረስ፣ በማከምና እንክብካቤ በማድረግ ታላቅ ሃገራዊ አበርክቶ ማበርከታቸውን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል፡፡


የምስጋናና እውቅና ፕሮግራሙ በመዘጋጀቱ በእጅጉ መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ የጦር ሃይሎች ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ናቸው፡፡

ፊልድ ማርሻል አክለውም ጤና ባለሙያዎች በጦርነት ጊዜ ልክ እንደወታደር ሆነው ነበር የዘመቱት፤ ሰራዊቱ ጉዳቱ እንዳይከፋ ተንከባክበው፣ አክመውና አድነውም ወደ መከላከያ እንዲመለስ በማድረግ ሃላፊነታቸውን ስለተወጡ በመከላከያ ስም አመስግነዋል፡፡

በእውቅና ፕሮግራሙ ለተሳተፉ አካላትም ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ለሁሉም ጤና ባለሙያዎች ምስጋና እንዲያደርሱላቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ 


የክልልና የከተማ መስተዳድር ጤና ቢሮዎች፣ የዞን ጤና መምሪያዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ዬንቨርሲቲዎችና ኮሌጆች፣ ደም ባንኮች፣ የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎቶች፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል፣ የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታሎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የዋንጫና የእውቅና ምስክር ወረቀት ከጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ፣ ከኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ከመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ ተበርክቶላቸዋል፡፡