አስራ ስድስተኛው የቲቢ ምርምር ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል

  • Time to read less than 1 minute
TB research

አመታዊ ብሔራዊ የቲቢ ምርምር ጉባኤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መደረጉ ጠቀሜታው የጎላ ነው ያሉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ አገራች ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት እና የተለያዩ ግጭቶች ምክንያት በጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመቶች እና የጤና ተቋማት መስተጓጎል፤ የህዝብ መፈናቀል፤ የድርቅ መስፋፋት እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያቶች በቲቢ በሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ላይ የተመዘገቡ ስኬቶች እንዳይቀለበሱ በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ 


በየአመቱ በሚካሄደው የቲቢ ምርምር ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ የምርምር ሥራዎች የቲቢ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 
አገራች ኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ ስርጭት ለመግታትና ቲቢ ለማጥፋት ዘመናዊ የምርመራ መሳሪያዎችን በጤና ተቋማት በማስገባት አገልግሎቱ ተደራሽ በማድረግና በየአምስት አመቱ የሚተገበር እቅድ በማዘጋጀት እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡ 


በኢትዮጵያ 151 ሺ የቲቢ ህመምተኞች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ታዬ ለታ፣ የጤና ሚኒስቴር የቲቢ በሽታ ኬዝ ቲም አስተባባሪ፣ ከነዚህ ውስጥም 110 ሺ ህመምተኞች ላይ የልየታ ስራ የተሰራ ሲሆን 40 ሺ የሚጠጉት ህሙማን ላይ አሁንም መድረስ አልተቻለም ብለዋል፡፡ 


ኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ ከተሰራጨባቸው 30 አገራት ውስጥ ምትገኝ የነበረ ሲሆን መድሃኒት የተላመደ ቲቢን አክሞ በማዳን ውጤታማ ከተባሉ አምስት አገራት አንዷ እንደሆነች የጠቆሙት አቶ ታዬ አሁንም በቲቢ በሽታ ምክንያት በየአመቱ ከ19 ሺ በላይ ዜጎች ውድ ህይወታቸውን ያጣሉ ብለዋል፡፡ 


በቲቢ በሽታ ላይ በተሰሩ የምርምር ስራዎች የበሽታው ስርጭት እንዲቀንስ ከማድረጉ ባሻገር ቀደም ሲል ከሁለት አመት በላይ ይሰጥ የነበረው የህክምና አገልግሎት ወደ አንድ አመት ዝቅ እንዲል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ተብሏል፡፡ 


በአለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ መድሃኒት በተላመደ ቲቢ ከፍተኛ ጫና ካለባቸው ሰላሳ አገራት መካከል አንዷ የነበረች እና አሁን በተሰራው ከፍተኛ ስራ ከዝርዝሩ መውጣቷን አቶ ታዬ ለታ ተናግረዋል፡፡ 


በአስራ ስድስተኛው የቲቢ ምርምር ጉባኤ ላይ ከ2022 እስከ 2026 እ.ኤ.አ ተግባራዊ የሚደረግ ሶስተኛው እትም ብሔራዊ የቲቢ የምርምር ፍኖተ ካርታን  የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ ይፋ አድርገዋል።


 ከመጋቢት 13 እስከ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ እየተደረገ በሚገኘው በዚህ ጉባኤ ፖሊሲ አውጭዎች፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ አጋር ድርጅቶች እንዲሁም  የጎረቤት አገራት እና የአገር ውስጥ ተመራማሪዎች  የሚሳተፉ ሲሆን በርከት ያሉ የምርምር ስራዎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡