በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተለያዩ  አገልግሎቶች ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄደ

  • Time to read less than 1 minute
Inauguration

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት ጥራት ያለው ህክምና ተደራሽነትን ለማሻሻልና  የስፔሻሊቲ እና ሰብ ስፔሻሊቲ ህክምና አገልግሎትን ለመስጠት የተለያዬ የህክምና ቴክኖሎጅዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልፀው በዛሬው እለትም በዋቻሞ ዩንቨርስቲ የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበት የተተከለ የሲቲ ስካን ማሽን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።


በተጨማሪም በሆስፒታሉ ለሚገነቡት የኦክስጅን ማምረቻና 450 አልጋ የሚይዝ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት መስጫ ማዕከል የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።


የዋና ዋና ከተሞች የድንገተኛ፤ አደጋና ጽኑ ህክምና አገልገሎት ማሻሻያ ፕሮግራም (Major city Emergency and Critical services Improvement Program(MECIP) በተመለከተም የቅድመ ጤና ተቋም የጥሪ ማዕከል አገልግሎትን አስጀምረዋል።


የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው፣ በዘርፉ ከፍተኛ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት፤ ዘመኑ ባፈራቸው ዘመናው የቴክኖሎጂ ውጤቶች የታገዙ ከፍተኛ የስፔሻሊቲ እና ሰብ ስፔሻሊቲ  ስልጠና በመስጠትና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ረገድ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ሚና እጅግ የላቀ መሆኑን ገልፀው ለዘርፉ መሳካትም በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡


በተጨማሪም የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ እንድሁም የፌደራል የክልልና የዞን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።