በኢትዮጵያ ሁለተኛ የሆነው የካንሰር ህክምና ጨረር አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተመረቀ

  • Time to read less than 1 minute
Inauguration

በኢትዮጵያ በየአመቱ ከሰባ ሺ በላይ ዜጎች በተለያየ አይነት የካንሰር በሽታዎች እንደሚጠቁ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ለእነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች የጨረር ህክምና አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ነበር፡፡


በዛሬው ዕለት የተመረቀውና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የጅማ ዩንቨርስቲ ሆስፒታል የጨረር ህክምና ማዕከል በከፍተኛ ወጪ መዘጋጀቱና አገልግሎት መጀመሩ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ላይ ብቻ ተወስኖ የቆየው የጨረር ህክምና አገልግሎት ጫናን በመቀነስ በህክምናው ተደራሽነት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል፡፡


በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንዳሉት የበሽታውን ስርጭትና አሁን ያለበት ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው ካለው ሀገራዊ ፍላጎትና እንዲሁም የጨረር ህክምና ለማግኘት ተመዝግበው የሚጠብቁት ታካሚዎች በርካታ እንደመሆናቸው መጠን አገልግሎቱን በቀጣይ ሰባት ማዕከላትን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለማስጀመር እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ሊያ አያይዘውም ይህ የጨረር የህክምና አገልግሎት እውን እንዲሆን የበኩላቸውን ሁሉ ያደረጉ ተቋማትና ግለሰቦችን አመስግነው በቀጣይ ህክምናውን ለማስፋፋት የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡ 


በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን መስራች የቀድሞ ቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ፣ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ፣ የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ነጂብ አባራያ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የማህበራዊና ፍትህ ዘርፍ ሀላፊ አቶ በቀለ መንገሻ፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ጀማል አባፊታ  የዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ኃላፊ ዶ/ር ኤልያስ አሊ ተገኝተው ማዕከሉን መርቀው ከፍተዋል፡፡