በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ አትዮጵያውያ የተሰባሰቡ መድኃኒቶች ጥቃት ለተፈጸመባቸው የህክምና ተቋማት ማሰራጨት ተጀመረ።

  • Time to read less than 1 minute
Donation

የጤና ሚኒስቴር ከዲያስፖራው ማህበረሰብ የተደረጉ ድጋፎችን በተቀናጀ መልኩ እንዲሰበሰብ፣ እንዲለይና በጦርነቱ ለተጎዱ ጤና ተቋማት ከተደለደለ በኋላ ስርጭቱ እንዲከናወን በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለየጤና ተቋማቱ ከየካቲት 04/2014 ዓ.ም ጀምሮ ስርጭት እያከናወነ ሲሆን  እስካሁንም ሸዋሮቢት፣ በአጣዮ ሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ፣ በከሚሴ ሆስፒታል፣ በኮንቦልቻ ሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ፣ በደሴ ሆስፒታል፣ በሰኞ ገበያ ጤና ጣቢያ፣ እና በቦሩ ሜዳ ሆስፒታል ድጋፉን ማድረስ ተችሏል። በመቀጠልም አፋር ክልልን ጨምሮ በተቀሩ አከባቢዎች የሚሰራጭ ይሆናል።


በዚሁ ድጋፍ ርክክብ ወቅት የደሴ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሀይማኖት አየለ እንደተናገሩት የደሴ ሆስፒታልን ወደቀደመ አገልግሎቱ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን የዲያስፖራው ማህበረሰብም ያደረገው እገዛ ምስጋና የሚቸረው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሆስፒታሉ ከገጠመው ፈተና አንፃር ከፍተኛ ስራ የሚጠይቅ በመሆኑ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ በተለይ የህክምና መሳሪያዎች እና የማይድኑ ህመሞች መድኃኒቶች ድጋፍ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ 


እንደ ዶ/ር ሀይማኖት ሁሉ የሌሎች ሆስፒታሎች ስራ ኃላፊዎችም ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይ የወደሙ ጤና ተቋማት የበለጠ ተቋቁመው ስራ እንዲጀምሩ የሁሉም ድጋፍና ርብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡


ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ እና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እገዛቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ ቀርቧል፡፡