ደሴ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ወደ አገልግሎት አሰጣጥ በመመለሱ መደሰታቸውን ተገልጋዮች ገለፁ

  • Time to read less than 1 minute
Community

በጦርነቱ ምክንያት ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ የህክምና አገልግሎት መስጠት በጀመረው የደሴ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግልጋሎት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ነዋሪዎች ገለፁ።


በሆስፒታሉ ሲገለገሉ ያገኘናቸው ወ/ሮ መሬሞ ሙሄ እና አቶ አበበ አብረሀም እንደገለፁት የሆስፒታሉ በሮች ተከፍተው ነጭ ገዋን የለበሱ የጤና ባለሙያዎች በፈገግታ ታካሚዎችን ሲያስተናግዱ በማየታቸው ተደስተዋል።


ህዳር 25/ 2014 ዓ ም በሆስፒታሉ እንድትገኝ ከሀኪሟ ቀጠሮ ተሰጥቷት እንደነበርና በነበረው ጦርነት ምክንያት እንዳላቀረበች የተናገራቸው መሬሞ ያ የስቃይ ጊዜ አልፎ ዛሬ ወደ ሆስፒታሉ በመቅረብ ተመርምራ መድሀኒት ሊታዘዝላት በመቻሉ ከጭንቀት እንደገላገላት መስክራለች።


እህቴን ለማሳከም መጥቼ ተገቢውን አገልግሎት አግኝቼ የራጅ ምርመራ ውጤት እየጠበቅን ነው ያለው አበበ በበኩሉ ለዚህ ብርሀናማ ቀን በመብቃታችን ፈጣሪንና መንግስትን አመሰግናለሁ ብሏል።


የደሴ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ልዑል መስፍን እንዳሉት ከወረራው በኋላ ሆስፒታሉ ስራ ከጀመረባቸው ቀናት አንስቶ እስከዛሬ ድረስ 1000 እናቶችን ማዋለዳቸውን ገልፀው ከነዚህ ውስጥ 153 የሚሆኑት በቀዶ ጥገና ከምጣቸው የተገላገሉ ናቸው ብለዋል።


በሆስፒታሉ ሚድዋይፈር የሆኑት አቶ አጥናፉ ሙሉጌታ በበኩላቸው የምንሰራበት መሳሪያ የለንም ብለን ለመቀመጥ የእናቶችና ህፃናት ስቃይ ዕረፍት የሚሰጠን አይደለም ካሉ በኋላ በወር እስከ 800 እናቶች የሚወልዱበት ሆስፒታል ስራ መጀመሩ ለኛም ዕፎይታ ነው ብለዋል።


በደቡብ ወሎ ዙሪያ ለሚገኙ የአፋር፣ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እና የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ጭምር አገልግሎት የሚሰጠው አንጋፋው የደሴ ሆስፒታል በአንድ ዓመት ብቻ እስከ 500ሺ ታካሚዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን በጦርነቱ ወቅት ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸውን ንብረቶቹን በዘረፋና በውድመት ማጣቱን ኃላፊው ተናግረዋል ።


በጦርነቱ የተጎዱ ሆስፒታሎቸ ከሌሎች ጋር ጥምረት ፈጥረው እንዲደጋገፉ በተቀየሰው አሰራር መሰረት የቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆሰፒታል የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችንና  መድሀኒቶችን በመለገስ እንዲሁም ሀክሞችና ሌሎች የጤና ባለሙያዎችን በጊዜያዊነት በመመደብ የደሴ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ወደ ስራ እንዲገባ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ሲሆን ጤና ሚኒሰቴር የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ ድርጅት እና ሌሎች አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር ተጨማሪ ድጋፎችን እንዲያኙ አድርጓል ።