"የእናቶችን ሞት ለማስቀረት ሁሉም አካላት ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ ሊሰሩ ይገባል!" ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ

  • Time to read less than 1 minute
Dr. Dereje Duguma

"በማንኛውም ሁኔታ ከወሊድ በሁዋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንግታ" በሚል መሪ ቃለ በአማራ ክልላዊ መንግስት ደሴ ከተማ በተከበረበት ወቅት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደተናገሩት በሀገራችን በቀን ከሰላሳ በላይ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ተናግረው እንደ ደሴ ባሉ በህውሀት አሸባሪ ቡድን የጦርነት ጥቃት እና ዘረፋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ችግሩ ሊከፋ እንደሚችል በመረዳት ሁሉም አካላት በከፍተኛ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

 
አሸባሪው ብድን የጤና ተቋማቱን ቢያወድሙና ቢዘርፉም ጠንካራ መንፈሳችንን ግን ሊነኩት አይቻላቸውምና ደግመን ተረባርበን በመገንባት ለእናቶችና ለሌሎችም የጤና አገልግሎቶችን በተሻለ እናቀርባለን ብለዋል፡፡  


የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የጤና ተቋማትን፣ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን፣ መድሀኒቶችን እና አስፈላጊ ግብአቶችን ማደራጀት በእጅጉ አስፈላጊ ነው ያሉት ዶ/ር ደረጀ ይህንን በማሟላት ረገድ የጤና ሚኒስቴር አጋር አካላትን በማስተባበር በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በህውሀት አሸባሪ ቡድን የተዘረፉትንና የወደሙትን የጤና ተቋማት ልዩ ትኩረት በመስጠት በመስራት ላይ እንዳለ አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የእናቶች ጉዳይ የጤና ሚኒስቴር እና የጤና ባለሙያው ብቻ ባለመሆኑ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ቀዳሚ አጀንዳቸው በማድረግ ሊሰሩ እንደሚገባ ጥሪ በማቅረብ የጤና ሚኒስቴር በቀጣይ አምስት አመታት የእናቶችን ሞት ትርጉም ባለው ደረጃ ለመቀነስ ስትራቴጂ መንደፉንም አስታውቀዋል፡፡ 


የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ዶ/ር ጋሹ ክንዱ በበኩላቸው በክልሉ የእናቶች ሞትን ለመቀነስ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ ቢሆንም አሸባሪ የህውሀት ቡድን በጤና ተቋማቱ ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ በመፈፀማቸው  ክልሉ የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ እያደረገ ባለው ጥረት ከፍተኛ ፈተና መደቀኑን አመልክተው ከነዚህ ችግሮች ለመውጣትና ጤና ተቋማቱ የቀደመ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ በከፍተኛ ርብርብ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም ተቋማቱ  በከፊልም ቢሆን ስራ ለማስጀመር የተቻለ ሲሆን በመሉ አቅም ህብረተሰቡን ማገልገል እንዲችሉ አቅም ያላቸው ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


በደሴ ከተማ በተከበረው የጤናማ እናትነት ወር ላይ መወያያ ሰነድ ያቀረቡት የጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና  ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም እናቶች በወሊድ ጊዜ በሚከሰቱ ሶስት መዘግየቶች ማለትም ወደ ጤና ተቋም እናቶች ባለመሄዳቸዉ፣ ለመሄድ ለወሰኑም ምቹ መሰረተልማት እና መጓጓዣ እጦት እንዲሁም በጤና ተቋም ከደረሱ በኋላ ጥራትና ፍትሀዊ አገልግሎቶች በሚፈለገው መልኩ ባለመኖሩ ምክንያት ህይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ተናግረው እነዚህን ሶስት መዘግየቶች ሊያስቀሩ የሚችሉ ስራዎችን በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ 


ከዚህ አኳያ ጤና ሚኒስቴር እናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል እንዲያደርጉ በሁሉም መዋቅሮች እየተሰራ ሲሆን፣ ወደ ህክምና ተቋማት ለማድረስ የሚረዱ አንቡላንሶችንም፣ የሰለጠኑ ማለሙያዎችን እና አስፈላጊ ግብአቶችን  በከፍተኛ መዋለ ነዋይ በመግዛት ለጤና ተቋማት የማዳረስ ስራ በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶችን በተለይ ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ የሚከሰት መዘግየትን ለማስቀየር አጀንዳ አድርገን በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ዶ/ር መሰረት በጤናው ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ሁሉም አካላት  አና ሌሎች ሴክተሮችም የእናቶችን ሞት መቀነስን ቀዳሚ አጀንዳ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡


በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው እና በድርቅ ምክንያት ለተጎዱ አካባቢዎችም ከፍተኛ ትኩረት መበስጠት ድጋፍ እንደሚደረግም ዶ/ር መሰረት አክለው ተናግረዋል።