"እናቶች በጤና ተቋማት በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲወልዱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት።"  ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ

  • Time to read less than 1 minute
Dr. Dereje Duguma

የጤናማ እናትነት ወር "በማንኛውም ሁኔታ ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶችን ሞት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንግታ" በሚል መሪ ቃል በአለም ለ35ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስተባባሪነት በአበበች ጎበና የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል ተከብሯል፡፡ 


የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በዓሉን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር በሀገራችን ከእናቶች ሞት ጋር ተያይዞ በተደረገው ጥናት በዓመት ከሚሞቱት እናቶች በተለይ 50 በመቶ የሚሆኑት ከደም መፍሰስ ጋር በተያያዘ ምክንያት መሆኑን ገልፀው እናቶች በጤና ተቋማት በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲወልዱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡ ለዚህም የሃይማኖት አባቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የኪነጥበብ ሰዎች፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ በመፍጠር እናቶች በህክምና ተቋም እንዲወልዱ እንዲያበረታቱ አሳስበዋል፡፡


የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው የእናቶችና ህፃናት ሞት እና በሪፈራል ምክንያት የሚከሰትን እንግልት ለመቀነስ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተው የአበበች ጎበና ሪፈራል ሆስፒታልን ጨምሮ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ስር በሚገኙ ሆስፒታሎች የተቀናጀ የሴቶችና ህፃናት እንክብካቤና ፍትህ ማዕከላት ተደራጅቶ ስራ እንዲጀምሩ እየተደረገ መሆኑ ጥቃት የሚደርስባቸው እናቶችና ህፃናት አገልግሎቱን ማግኘት እንዱችሉ ማስቻሉን  ገልፀዋል፡፡


በአዲስ አበባ አምስተኛው የተቀናጀ የሴቶችና ህፃናት እንክብካቤና ፍትህ ማዕከል በሆስፒታሉ በዕለቱ ተመርቋል፡፡