በጦርነት እና በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የስነ አዕምሮ እና የስነ ልቦና ህክምና  ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በጤና ሚኒስቴርና በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር የተዘጋጀ የዘርፈ ብዙ ምላሽ እቅድ ይፋ ተደረገ

  • Time to read less than 1 minute
ministers

በተለያዩ ክልሎች በጦርነት እና በተፈጠሩ ግጭቶች ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የተቀናጀ  የስነ አዕምሮ እና የስነ ልቦና ህክምና ምላሽ  በመስጠት እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ይበልጥ ለማጠናከርና ፈጣን ለማድረግ የጤና ሚኒስቴር እና የሴቶችና  ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት እቅድ ለባለድርሻ አካላት በኢትዮጵያ የህረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች የመልሶ ማቋቋምና ሪዚሊየንስ ዳይሬክተር በሆኑት በዶ/ር ያረጋል ፉፋ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።


በቅንጅታዊ  ርብርቡ የስነ አዕምሮ ፣  የስነ ልቦና እና የማህበራዊ ስራዎች እንዲሁም ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የመፍጠር ተግባራት እንደሚከናወኑ በእቅዱ የተካተቱ ዝርዝር አላማዎች ያሳያሉ፡፡ 


እቅዱ በዋናነት በማህበረሰብ ደረጃ ድጋፍ የሚሰጡ  ልዩ ልዩ ሙያ ያላቸውን ቡድኖች አሰልጥኖ ማሰማረትን፣ በጤና ተቋማት የሚሰጡትን የስነ እዕምሮ ጤና አገልግሎት ማጠናከርን እና በጾታዊ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች በጤና ተቋማትና ከጤና ተቋማት ውጪ የጤና እና ስነ ልቦና ድጋፍ አገልግሎት የሚያገኙበትን ስርዓት ማጠናከር ለዚህም ስራ ውጤታማነት ሰፊ የባለሙያዎች ቁጥር አሰልጥኖ ማሰማራትን ያካተተ ነው።


በመድረኩ ላይ ከመንግስት አመራሮች፣ ከሙያ ማህበራት፣ ከሀይማኖት ጉባኤ፣ ከዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ባለሙያዎች እና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች የተገኙ ሲሆን ተሳታፊዎቹ የቀረበውን እቅድ ሊያዳብሩ የሚችሉ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡


በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን የገለፁት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ  የሚታዩና የማይታዩ በርካታ ጉዳቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ የሚጠበቀው የድጋፍ ስራም በጣም ሰፊ መሆኑን አስረድተው ችግሮችን እንደ አንገብጋቢነታቸው ቅደም ተከተል በማስያዝ ባለው አቅም ቶሎ ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡   


የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው እንደተናገሩት የአዕምሮና ስነ-ልቦና ችግሮች፣ የመሰረተ ልማቶች ውድመት እና የእሴቶች መሸርሸር ጠለቅ ያሉ ስራዎችን እንደሚጠይቁ  የገለፁ ሲሆን የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ እቅዱን ለመተግበር የሚመደበው የሰው ኃይል እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሞራል ልዕልና መስራት በጣም ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል፡፡