ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ለማቋቋምና መልሶ ስራ ለማስጀመር እንዲቻል ከጤና ሚኒስቴር የቀረበ  ሁሉን-አቀፍ የድጋፍ ጥሪ!

  • Time to read less than 1 minute
Health Facility

አሸባሪው የጥፋት ቡድን ህወሓት በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ካደረሰው ሰብዓዊና ሞራላዊ ጥፋት በተጨማሪ  ህዝብ የሚገለገልባቸውን የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቀቋማት፤ የህክምና ግብዓት ማከማቻ ተቋማትን እና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት አውድሟል፡፡ የህክምና መሳርያዎችን እና ሌሎች ግብዓቶችንም ጭኖ በመውሰዱ ዝርፍያ እና ጉዳት ፈጽሟል፡፡

 
በጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ወድመት በተለይ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የመሰረታዊ እና ድንገተኛ ህክምና አግልግሎት አሰጣጥ በእጅጉ አስተጓጉሏል። እስካሁን በደረስንበት መረጃ ከ2700 በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማት አገልግሎት የማይሰጡ ሲሆን በአሁን ወቅት በመንግስት ተደራሽ ያልሆኑ አከባቢዎች ሲካተቱ ዉድመት የደረሰባቸዉ ቁጥር ከዚህ እንደሚያሻቅብ ይጠበቃል።


በጤና ተቋማቱ ላይ በተከሰተዉ መጠነ ሰፊ ወድመት፤ ምክንያት በጣም በርካታ ዜጎቻችን የጤና አግልግሎት የሚያገኙበት በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ተስተጓጉሏል፡፡ በሌላም በኩል ግጭቱ በተከሰተባችዉ አካባቢዎች አቅራቢያ አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች እንዲጨናነቁ እና መደበኛ ከሆነዉ አቅማቸዉ በላይ አገልግሎት እንዲሰጡ አስገድዷል። በመሆኑም ለህብረተሰቡ ቀጣይነት ያለዉ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል እና አገልግሎቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ  ሁሉንም ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ያሳተፈ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ጥሪ ማድረግና የመልሶ ማቋቋሚያ ሀብት ማሰባሰብ እጅጉን አስፈላጊ ሁኖ ተገኝቷል፡፡

 
ጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለዚህ  አደጋ ምላሽ ለመስጠት እንዲያግዝ ሁሉቀፍ ከግጭት ጋር የተያያዘ ድንገተኛ አደጋ የጤና ምላሽ ስርዓት አቋቁሞ ዘርፈ ብዙ  ርብርብ እያደረገ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም ይህን ፈታኝ የሆነ ተግዳሮት ለመግታት ዝርዝር ተግባር ያለው ስትራተጂ በመንድፍ ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን ከእነዚህም የመጀመሪያዉ እና በአሁን ወቅት እየተሰራበት ያለዉ የተዘረፉ እና ዉድመት የደረሰባቸዉን ጤና ተቋማት ከተለያዩ በሃገር አቀፍ ደረጃ ካሉ  የመንግስት ተቋማት ጋር በማጣመር  ተቋማቱን መልሶ ማቋቋም እና ስራ ማስጀመር  ይገኝበታል፡፡ 


አሁን ላይ ከውድመቱ ከፍተኛነትና የጤና ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑና ለማህረሰባችን የምሰጠውን ጤና አገልግሎት በፍጥነት መሰጀመር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የተደራጀ ድጋፍ ከሁሉም አቅጣጫ ማሰባሰብ ከመቼዉም ጊዜ በላይ እና ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነዉ፡፡


የጤና ሚኒስቴር በግጭቱ አካባቢ ፈጣን ዳሰሳ በማካሄድ አሁን ላይ  የወደሙ የጤና  ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እና ስራ ለማስጀመር  እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚስፈልግ እነደሆነ በዳሰሳው ግኝት አመላክቷል፡፡  ይህንን የሃብት ማሰባብሰብ እና ድጋፍ ስራን ለማስተባበር የጤና ሚንስቴር የባለሙያ ቡድን ያቋቋመ ሲሆን  በግለሰብም ሆነ በቡድን ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ  አስፈላጊ መረጃ እና ትብብር ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን እንገልጻለን። ስለሆነም በሃገር ዉስጥ ሆነ ከሃገር ዉጭ ያሉ መላዉ ኢትዮጲያዊያን ፤ የኢትዮጲያ ወዳጆች፤ የግሉ ዘርፍ፤ ለጋሽ ድርጅቶች፤ አጋር ድርጅቶች፤ ሲቪክ ማህበራት፤ የሙያ ማህበራት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይህን ሃገር አቀፍ የወደሙ የጤና ተቋማት ማቋቋምና ስራ ማስጀመር  ጥሪ ተቀብላችሁ በሁሉም አይነት ድጋፍ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።


ድጋፍ ለማድረግ በኦንላይን ድህረገጽ https://www.moh.gov.et/site/donations መጠቀም የምትችሉ ሲሆን አስፈላጊውን ተጨማሪ መረጃ በኢሜይል አድራሻ moh@moh.gov.et , abnet.zeleke@moh.gov.et ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን።