በከፍተኛ ወጪ ተገንብተው አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ  የደሴና የኮምቦልቻ ጤና ተቋማት በአሸባሪውና ወራሪው የህውሃት ቡድን አገልግሎት እንዳይሰጡ ሆነው ወድመዋል፡፡      

  • Time to read less than 1 minute
health facility

በደሴ ከተማ የሚገኘው የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአሸባሪውና ወራሪው የህውሀት ቡድን አገልግሎት እንዳይሰጥ ሆኖ የወደመ ሲሆን ቡድን በተደራጀ መልኩ የህክምና መሳሪያዎችንና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን ጭኖ ከመውሰዱ ባለፈ የቀሩትንም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አድርጎ ሙሉ በሙሉ አውድሟቸዋል።


ከእነዚህም መካከል በተኝቶ ህክምና፣ በፅኑ ህክምናና በአንስተኛና በከፍተኛ የቀዶ ህክምና ክፍሎች የነበሩ በብዙ ሚሊዮን ብር የተገዙ የትንፋሽ መስጫ /ventilator/ እና አንስቴዥያ ማሽኖች የተወሰዱ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በመውደማቸው በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት በማይችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል።


የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የ80 አመት ታሪክ ያለውና ለትግራይና ለአፋር አጎራባች ክልሎች ጭምር አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በዓመት ከ450 ሺ ህዝብ በላይ አገልግሎት ይሰጣል። 
በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው የኮምቦልቻ አጠቃላይ ሆስፒታልም ተመሳሳይ ውድመትና ወረራ ተፈጽሞበታል፡፡ ሆስፒታሉ 200 አልጋ የነበረው ሲሆን በቅርቡ በቀድሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር እና በጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ በተገኙበት ተመርቆ አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ነው፡፡ 


በተጨማሪም ከመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ቅርንጫፎች መካከል አንዱ የሆነው የደሴ ቅርንጫፍ በሽብርተኛው እና ወራሪው የህወሃት ቡድን ከፍተኛ ዝርፊያ እና ጉዳት ደርሶበታል፡፡ የጥፋት ቡድኑ በክምችት የነበሩ መድኃኒቶችን እና ሌሎች የህክምና ግብዓቶችን የቻለውን በመዝረፍ እንዲሁም የመስረተ ልማት አውታሮች ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል፡፡ 


ቅርንጫፉ ለ27 ሆስፒታሎች፣ ለ303 ጤና ጣቢያዎች፣ ለ60 ወረዳዎች እንዲሁም ከህግ ማስከበር ዘመቻው እስከ የህልውና ዘመቻው ድረስ በከፍተኛ ደረጃ የመድኃኒት እና ሌሎች የህክምና ግብዓት በማቅረብ አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ሲሆን በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የተገነባ ግዙፍ የእናቶች እና የህፃናት ክትባት ግብዓት ማከማቻ የማቀዝቀዣ ሰንሰለት መጋዘን (Cold Room)፣ ዋና ማጋዘን (Main Warehouse)፣ ቢሮዎች፣ የማከማቻ መሰረተ ልማት፣ ፎርክሊፍቶች ፣ የደህንነት መቆጣጠሪያ ስርዓቶችን፣ የቢሮ መሳሪያዎች እና ሌሎች ንብረቶችን አውድሟል፡፡