ጠንካራ የፋይናንስና ፍትሃዊ የጤና ስርዓቶች ጥራት ላለው የጤና አገልግሎት

  • Time to read less than 1 minute
discussion

በጅግጅጋ በሚካሄደው የጤናው ዘርፍ ልማት ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎ ተሳታፊዎች በተለያዩ ጤና ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት አካሂደዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ እና የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰሃረላ አብዱላሂ የተገኙበት የፓናል ውይይት የጤና ፋይናንስን እና ፍትሃዊነትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡


የጤና ፋይናንስ ስርዓቱን አስመልክቶ በቀረበው ፓናል ውይይት ከሃገር አቀፍና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሃብት ማሰባሰብ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን መንግስት ከጠቅላላው በጀት ውስጥ 13 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆነውን ለጤናው ዘርፍ እንዲመደብ ለማድረግ ተችሏል፡፡  
የግሉን የጤና ዘርፍና የመንግስትን ትብብር ለማጠናከር በተሰራው ስራ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በተለይም የጤና ግብአቶች ምርትና ተርሸሪ ኬር ላይ እንዲጨምር ማድረግ መቻሉ በውይይቱ ተነስቷል፡፡ 


የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎትም ባለፉት አስር ዓመታት ውጤት መመዝገቡ ተወስቷል፤ በዚህም በ2012 ዓ.ም ሲተገበርባቸው ከነበሩ 771 ወረዳዎች በ2013 ዓ.ም ወደ 834 ማሳደግ መቻሉን፣ ከ8.7 ሚሊዮን አባወራዎች/እማወራዎች በላይ አባል ማድረግ መቻሉን እና ከ40 ሚሊዮን በላይ ቤተሰቦች ተጠቃሚ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡  


ባለፈው በጀት ዓመትም ወደ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ደግሞ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ከአባላት የተሰበሰበ ነው፡፡ ጤና መድህን ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ የጤና አገልግሎቱ እና የተጠቃሚው ቁጥር መጨመሩ፣ መክፈል የማይችሉ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን አባወራዎች/እማወራ እንዲሁም ወደ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ቤተሰቦች ተጠቃሚ መሆናቸው በውይይቱ ቀርቧል፡፡

 
የኦሮሚያ ክልል የጤና ፋይናንስ ስርዓት ተሞክሮ በውይይቱ ሲቀርብ እንደተገለጸውም በጤና ተቋማት የማህበረሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ ሃብት ማሰባሰብ መቻሉን፣ ከግብዓት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የመድሃኒት አቅርቦት ለመቅረፍም ወደ 32 የማህበረሰብ ፋርማሲዎችን ማቋቋሙና በክልሉ ለጤና የሚመድበው በጀት በየዓመቱ እያደገ መምጣቱ በተሞክሮ ቀርቧል፡፡ 


በጤና ስርዓቱን ለማሻሻል ደግሞ በተግዳሮትነት የቀረቡም ነበሩ፤ ለአብነትም የጤና ተቋማት ዝግጁነት ማነስ፣ የመረጃ ስርዓቱ ዲጂታላይዝ አለመሆኑ፣ የጤና አገልግሎት ጥራት መጓደልና አገር አቀፍ የጤና ፋይናንስ ስርዓት ስትራቴጂ አልቆ ወደ ተግባር አለመገባቱ ተጠቅሰዋል፡፡

 
የጤና ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ አስመልክቶ በተካሄደው ውይይትም በሃገር አቀፍ ደረጃ በጤናው ሴክተር፣ በቤኒሻንጉል ክልል፣ በአጋር አካላትና በዓለም ጤና ድርጅት ያለው ተሞክሮ የቀረበ ሲሆን የጤና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ያስችል ዘንድ የፍትሃዊነት እስትራቴጂክ ዕቅድ ተነድፎ ወደስራ የተገባ መሆኑንና በዕቅዱ መሰረትም በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በጾታ፣ በኢኮኖሚ፣ ልዩ ድጋፍ የሚያስፍልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እና በሌሎች ምክንያቶች የሚመጣን ኢ-ፍትሃዊነት መቅረፍ በሚያስችል መልኩ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተነስቷል፡፡ 


ከዚህ ጋር ተያይዞም በአፈጻጸማቸው ዝቅተኛ በሆኑ እና የተለዬ ድጋፍ ለሚያስፍልጋው ክልሎች እና ዞኖች የቴክኒክ፣ የገንዘብና ሌሎች ድጋፎች መሰጠቱንና በመስክ ጉብኝቱ የታየው የተንቀሳቃሽ የጤና ቡድን አገልግሎቱ ለአብነት ቀርቧል፡፡ 


የጤና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በጤና ሴክተር ብቻ ማሳካት እንደማይቻል ታምኖበትም የተለያዩ መስሪያ ቤቶች /Multi Sectoral Approach/ በጋራ ተቀናጅተው ለመስራት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስተያየት ቀርቧል፡፡