በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የጥፋት ቡድኑ ባደረሰው ጉዳት ተፈናቅለው ባህርዳር ለሚገኙ ወገኖችና በክልሉ ውስጥ  ጉዳት ለደረሰባቸው  15 ጤና ጣቢያዎች  ድጋፍ ተደረገ 

  • Time to read less than 1 minute
Amhara

በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴአታ ወ/ሮ ሠሐረላ አብዱላሂ የተመራ ከጤና ሚኒስቴር፤ ፌዴራል ሆስፒታሎችና ከተጠሪ ተቋማትና ከግሉ ዘርፍ የተውጣጣ ቡድን በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ በህውሃት የጥፋት ቡድን ባደረሰባቸው ጉዳት ተፈናቅለው ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን ጎብኝቷል።

 
ቡድኑ ከደሴና ኮምቦልቻ አከባቢ በፀጥታው ችግር ምክንያት ተፋናቅለው በባህርዳር ከተማ በዘንዘልማ የተፈናቃዮች መጠለያ የሚገኙትን የጎበኙ ሲሆን በከተማው አስራ አራት ሺ አምስት መቶ ሃያ ሁለት ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃይ ወገኖች እንደሚገኙና በመጠለያ ቦታው አራት ሺ ሁለት መቶ ሃምሳ ሁለት ተፈናቃዮች የሚገኙ መሆኑ ታውቋል፡፡ ለተፈናቀሉ ወገኖች የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የክልሉ ጤና ቢሮ ባለሙያዎችን መድቦ ክሊኒክ የከፈተላቸው ሲሆን ከተፈናቀሉ የጤና ባለሙያዎች እና አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የህክምና አገልግሎትና የማልኑትሪሽን ችግር ልየታ ስራ እየተሰራ መሆኑን መመልከት ተችለዋል። 


በአገልግሎት አሰጣጥና በመድሃኒት አቅርቦት ዙሪያ ያገጠሙ ችግሮችን አስመልክቶ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከክልሉ ጤና ቢሮና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት በፍጥነት ችግሩ እንዲቀረፍ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ 


የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ ወ/ሮ ሠሐረላ አብዱላሂ  የተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መጎብኘታቸውን ገልጸው፤ የጤና አገልግሎትን ለማጠናከር  የሚያግዙና 15 ጤና ጣቢያዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችል 3.9 ሚልዮን ብር የሚያወጡ የህክምና ማገልገያ መሳሪያዎችን  ለክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ያስረከቡ ሲሆን በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተናግሯል፡፡ 


የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ድጋፍ ልባዊ ምስጋና በማቅረብ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከርና ከፌዴራል የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። 


የጉብኝቱ አካል የነበሩት የግሉ የጤና አገልግሎት ዘርፍ ተወካዮች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የተጎዱ ዜጎች ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። የፌደራል ሆስፒታሎችና ተጠሪ ተቋማቶች ከዚህ ቀደም የጀመሩትን ድጋፍ  በማጠናከር  አስፈላጊውን የሰው ሃይልና የግብዓት አገልግሎት መደገፍ፤ ማገዝ እና አብሮ ለመስራት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።