የዘንድሮው የጤና ዘርፍ አመታዊ ጉባኤ ‹‹ጠንካራ የጤና ፋይናንስ ለዘላቂ የጤና ልማት›› በሚል መሪ ቃል መካሄድ ጀምሯል፡፡
መንግስት ጤናማ ዜጋ የምርታማ ማህበረሰብ መሰረት መሆኑን በመገንዘብ ለጤናው ዘርፍ ትኩረት መስጠቱን የተናገሩት በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የእለቱ የክብር አንግዳ የአዲስ አበባ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ፤ በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የጤና መሰረተ ልማት እና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና አገልግሎትን በማስፋፋት ላይ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ክብርት ከንቲባ አዳነች በ2015 የበጀት አመት በአዲስ አበባ ከተማ በጤናው ዘርፍ የተሰሩ ተግባራትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ከከተማ አኗኗር ጋር የሚከሰቱ የጤና ችግሮች ልዩ ትኩረት እንደሚሹ የተናገሩት ከንቲባ አዳነች፤ ከከተማዋ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የሚያስፈልጉ የጤናማ አኗኗርን የሚያበረታቱ እርምጃዎችን መስተዳድሩ እየወሰደ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የጤናው ዘርፍ ቀጣይ የ3 አመት እቅድ መዘጋጀቱን አስታወቀዋል፡፡ ባሳለፍነው 2015 የበጀት አመት እንደ ግጭቶች እና ወረርሽኞች በጤናው ዘርፍ ላይ ተግዳሮት የፈጠሩ ቢሆንም በዘርፉ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ዶ/ር ሊያ አስረድተው፤ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ጤና ሚኒስቴር እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
በጤና ዘርፍ የተካሄዱ ዋና ዋና ተግባራት ዝርዝር በዶ/ር ሊያ የመክፈቻ ንግግር የተካተተ ሲሆን፤ የጤና ፋይናንስ የዘንድሮው ጉባኤ ትኩረት መሆኑን እና የጤና ፋይናንስን ለማሻሻል የመዋቅር ክለሳ እና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም በንግግራቸው አብራርተዋል፡፡
የእናቶች እና ህጻናት ጤና፣ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ማቋቋም፣ እና ወረርሽኞችን መቆጣጠር ላይ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ፤ ይህም እንዲሳካ መሰረት የሆኑትን የጤና ባለሞያዎችን እና ባለድርሻ አካላትን ያመሰገኑት ሚኒስትር ሊያ፤ ሁሉም የጤናው ዘርፍ አካላት በመተባበር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጤናው ዘርፍ ጉባኤ መልካም ተሞክሮዎችን የምንጋራበት እንደሚሆን የተናገሩት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክ/ሃላፊ ዶ/ር ሙሉጌታ እንዳለ፤ ጤና ቢሮው ከከተማዋ እድገት አኳያ የአገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ ፕሮግራሞችን እየተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ጤና ሚኒስቴር ያቀዳቸውን ግቦች እንዲያሳካ በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት የገለጹት ደግሞ የኤችኤንፒ ተወካይ ስኮት ሆክላንደር ሲሆኑ፤ በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ በተለይም በማህበረሰብ ጤና፣ በጤና ፋይናንሲንግ፣ እና የግል የጤና ዘርፍ ተሳትፎ እድገት መታየቱን መገንዘባቸውን ተናግሮ የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ዛሬ በተጀመረው ጉባኤ በጤና ዘርፍ በቁርጠኝነት አግልግሎት ላበረከቱ ባለሞያዎች እውቅና የተሰጠ ሲሆን፤ የጤና አውደ ርእይም በተሳታፊዎች ተጎብኝቷል፡፡
በዘንድሮው ጉባኤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሚኒስትሮች እና ሚኒስትር ዲኤታዎች፣ የሞያ እና የሲቪክ ማህበራት፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ ተጠሪ ተቋት፣ እና የአጋር ድርጅቶች ተወካዮችን ጨምሮ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል፡፡